በምስራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት በ39 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ ይተከላል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት በ39 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ ይተከላል
ነቀምቴ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት በ39 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ እንደሚተከል የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የቡና ምርት ቡድን መሪ አሰፋ መኮንን እንደገለጹት፤ በዞኑ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተተገበረ ባለው ኢኒሼቲቭ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል።
በተያዘው ዓመት ክረምትም በ39 ሺህ 983 ሄክታር መሬት ላይ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 279 ሺህ 632 የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
ችግኞቹም በመንግስት፣ በማህበራትና በአርሶ አደሮች የችግኝ ጣቢያዎች እንዲባዙ ተደርጎ በአሁኑ ወቅት ለተከላ ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።
ከችግኝ ዝግጅትና ተከላ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረምም የባለሙያዎች የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰጠ ነው።
የቡና ምርትና ምርታማነትን በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ያረጀና ምርት የማይሰጥ የቡና ተክል ጉንደላ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው የተጎነደሉ ተክሎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሰው ምርት የሚሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ የጉቶ ጊዳ ወረዳ አርሶ አደር ሹምዬ ባይሳ እና አርሶ አደር ገመቹ ደረጄ በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ያመርቱ ስለነበር በሚፈለገው ልክ መጠቀም እንዳልቻሉ ገልጸዋል።