የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ መከፈት የኢትዮጵያን የውጭ ምርት ጥገኝነት ከመቀነስ ባሻገር ኢትዮጵያን በዘርፉ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን መርቀዋል።
በሞጆ ከተማ በግራንዴር ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው የሴራሚክና የፖርሲሌን ንጣፎች ማምረቻ ፋብሪካ፣ ከዕቅድና መሬት ዝግጅት እስከ ሙሉ ሥራ ማስጀመር የወሰደው ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ገልጿል።
መሰረተ ልማቱ በ300,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ ፋብሪካ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀና ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ-ነዋይ የወጣበት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ክንውን መሆኑ ተመላክቷል።
በአሁኑ ወቅት 60x60 የሴራሚክ ንጣፎችን በስፋት ማምረት የጀመረው ይህ ፋብሪካ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የምርት ዓይነቶቹን በማስፋት የ80x80bg፣ 60x120፣ 70x140 እና 80x160 መጠን ያላቸውን የንጣፍ ዓይነቶች እንዲሁም የአውሮፓን የጥራት ደረጃ ያሟሉ የፖርሲሌን ምርቶችን ማቅረብ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ለፋብሪካው ምርት የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች 80 በመቶ የሚሆነው ከፋብሪካው በ100 ኪሎ ሜትር ክበብ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ የተቀናጀና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተሳሰረ የአቅርቦት ሰንሰለት መፍጠር ተችሏል።
ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ባሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ4.85 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን በቻለችበት በዚህ ወቅት፤ የግራንዴር ሴራሚክ መከፈት የውጭ ምርት ጥገኝነትን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላትም ጭምር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።