ካርዳችንን በጥንቃቄ በመያዝ የምንፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል -የገንዳ ውሃ ከተማና የጋዚግብላ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ካርዳችንን በጥንቃቄ በመያዝ የምንፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል -የገንዳ ውሃ ከተማና የጋዚግብላ ወረዳ ነዋሪዎች
ሰቆጣና ገንዳውኃ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በጠቅላላ ምርጫው ለመሳተፍ የወሰድነውን ካርድ በጥንቃቄ በመያዝ ለሁሉም የሚጠቅም ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በአማራ ክልል የገንዳ ውሃ ከተማና የጋዚግብላ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በወሰድነው ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ለህዝብና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ለመሳተፍ የወሰድነውን ካርድ በጥንቃቄ በመያዝ ለሁሉም የሚጠቅም ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ እንመርጥበታለን ብለዋል።
ከገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዮሴፍ አየነው የመምረጥ መብቴን ተጠቅሜ የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ያወጣሁትን ካርድም ለህዝብ ተጠያቂ የሚሆንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ይገነባል ብዬ ለማምነው ፓርቲ ድምጽ በመስጠት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት እውን መሆን የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ቤዛ አለሙ በበኩላቸው ሰላምና ዴሞክራሲን ለሚያሰፍን ፓርቲ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
"ካርዴን በወቅቱ ወስጃለሁ፤ በምርጫው ቀን በጠዋት ተገኝቼ ድምፄን በመስጠት ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዋግ ኽምራ ዞን የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ምስጋናው መኮነን ያወጡትን ካርድ አርሶ አደሩን የሚጠቅም ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
"የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ሰላም ወሳኝ ነው" ያሉት አርሶ አደሩ የአካባቢያቸውን ሰላም በንቃት በመጠበቅና የመኸር እርሻ ዝግጅታቸውንም እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
"የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያለው ቅስቀሳ የሚበጀንን ፓርቲ ለመለየት አግዞናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ደባሽ ናቸው።
ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የአካባቢያቸውን ሰላም አፅንተው እየጠበቁ መሆኑን ጠቁመው በድምፅ መስጫው ቀን ማልደው በመነሳት ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።