ቀጥታ፡

ለጠቅላላ ምርጫው በስኬት መጠናቀቅ የበኩላችንን እየተወጣን ነው

ግንቦት፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ ህብረተሰቡን በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ምርጫ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት በመሆኑ፣ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።


 

በባሌ ዞን የሮቤ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎቹ አቶ ኡመር ገመዳ እና አቶ በሺር በከር ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሀገር ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ኃላፊነት አለብን ብለዋል።


 

ለምርጫው ስኬታማነት ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙና ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።


 

የሃይማኖት አባት የሆኑት አባ ጥበቡ ቁምላቸው ህብረተሰቡ በጠቅላላ ምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ የማንቃትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኢሉባቦር ዞን ሀሉ ወረዳ የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው፣ በምርጫ ካርዳችን የምንሰጠው ድምፅ የሀገራችንንና የልጆቻችንን የነገ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ብለዋል።


 

አቶ ሳህለ ጉተማ እና አቶ ኃይሉ መኮንን በወሰዱት የመራጭነት ካርድ የሀገርንና የልጆቻቸውን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በነፃነት የሚጠቀሙበት ሀገራዊ ሁነት በመሆኑ፣ በመራጭነት የሚሳተፉ ዜጎች የድምፃቸውን ዋጋ ለሀገራቸው መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ወጣቶች ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ወጣት ኦብሳ መሐመድ እና ወጣት ቡርቃ አሊዪ ምርጫ የሀገር የወደፊት ተስፋ የሚወሰንበት በመሆኑ እንደ አንድ ወጣት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።

ምርጫው የወጣቶችን የልማት ተጠቃሚነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።


 

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሙርቴሳ መሐመድ በበኩሉ፤ በዞኑ ለሚገኙ 70 ሺህ ወጣቶች አስፈላጊው ቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አስታውቋል።

ማህበሩ ወጣቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባለፈ 2 ሺህ 756 የምርጫ ታዛቢዎችን መመደቡንም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም