የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እያሳለጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እያሳለጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እያሳለጠ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 85 ሚሊየን በላይ ሰዎች ስልጠና በመውሰድ የሰርተፍኬት ባለቤት እየሆኑ እንደሚገኝም አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ስልጠናን ሐምሌ 2016 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ተነሳሽነት ወጣቶች ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ያለመ የዲጂታል ክህሎት ማልሚያ መርሃ ግብር ሆኖ እያገለገለ ሲሆን በዚህም ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥት ጋር በመተባበር ያስጀመረው የኢትዮ-የኮደርስ ስልጠናም ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በማፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ስልጠናውም ዜጎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ዳታ አናሊሲስ፣ በአንድሮይድና በፕሮግራሚንግ ዴቨሎፕመንት ዋና ዋና ዘርፎች ስልጠና የሚያገኙበትን ምኅዳር ፈጥሯል።
ስልጠናው በኦላይን ሥርዓት በነፃ የሚሰጥና ዜጎች ያለ ዕድሜ ገደብ መሠረታዊ የዲጂታል ስልጠና ወሰደው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ሰርተፍኬት ያገኙበታል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓትን በመገንባት ሂደትም በርካታ ዜጎችን የቴክኖሎጂ ክህሎት በማስታጠቅ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
ይህም የኢትዮጵያን የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲ ብዝኅ የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያሳልጥ ሀገር በቀል የዲጂታል ክህሎት የታጠቀ ትውልድ በማፍራት እያስቻለ ነው።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ስዩም መንገሻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል ሥነ-ምኅዳር ተፈጥሯል።
ለአብነትም የአምስት ሚሊየን የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በርካታ ዜጎች የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የሚታጠቁበትን አስቻይ የአሰራር ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረ አንስቶም እስካሁን ከ4 ነጥብ 85 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስልጠናው አካል በመሆን የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ባለቤት እየሆኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለፈጠራና ቴክኖሎጂ ልማት የተሰጠው ትኩረትም የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያሳልጥ የሰው ሃይል ማፍራት እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናም የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የስልጠና መርሃ ግብሩም ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኦላይን ሥርዓት ዕውቀት የሚሸምቱበትን ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በቀሪ የሥልጠናው ጊዜያትም ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆን የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት ማዳበር እንደሚችሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።