ቀጥታ፡

በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ስኬቶች ተመዝግበዋል - አቶ ጌቱ ወዬሳ

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ) ፦ በሀረሪ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ይሄንን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ባለፉት አምስት አመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በሌሎችም የልማት መስኮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲው ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊነትን በተግባር በማረጋገጥ ቋንቋ እና የጋራ ማንነትን ለኢትዮጵያ ብልፅግና ምሶሶ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ፓርቲው ለህዝብ የገባውን ቃል ዕውን በማድረግ ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገቡንም ገልጸዋል።

በፖለቲካ ረገድ ከፓርቲው ምስረታ በኋላ በክልሉ ከሴራ ፖለቲካ ወደ መርህ ፖለቲካ፣ ከመገፋፋትና ከጥላቻ ወደ ሰላምና አብሮነት እንድንሸጋገር አድርጎናል ብለዋል።

ፓርቲው ከልዩነት አንድነትን፣ ካለፈ ጥላቻና ቁርሾ የነገ ተስፋን፣ ትብብርና ኅብረትን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።

በኢኮኖሚ ረገድም በግብርና እና በቱሪዝም ልማት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም የትምህርት ጥራትን ከማጎልበትና የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ እና በከተማው በተሰራው የኮሪደር ልማት፣ በከተማ እና በገጠር የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም ፓርቲው ለሰው ተኮር ስራዎች የሰጠው ትኩረት የዜጎችን ችግር በማቃለል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ፍትሀዊ ፤ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል።

በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ለማስቀጠል ግንቦት 24 ቀን በሚካሄደው 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና የክልሉ ነዋሪዎች ብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም