ወጣቶች በሀገራዊ ብልፅግና ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በሀገራዊ ብልፅግና ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት ወጣቶችን በሀገራዊ ብልፅግና ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው፤ ዛሬ "ወጣት ይምረጥ ኢትዮጵያ ትጽና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና አሻራ በተቀመጠበት ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከመላ ከተማዋ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም መካሄዱን አመልክተዋል።
ስለ ወጣቱ ተጠቃሚነት ችግርን እያወራን ሳይሆን ቀንና ሌሊት እየሰራን ለችግሩ ተግባራዊ ምላሽ ከሰጠንባቸው እና ተጠቃሚነቱን ካረጋገጥንባቸው ስፍራዎች አንዱ በሆነው በገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ70 ሺህ በላይ ከሆኑ የከተማችን ወጣቶች ጋር በስፖርታዊ እንቅስቃሴ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።
ባለፉት 5 ዓመታት የሰራናቸው የልማት አሻራዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት የሚመሰክሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ከማንም በላይ ሀገር እየተገነባች ያለችው ለወጣቶቻችን በመሆኑ የብልፅግናዋ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ብለዋል።
የከተማችን ወጣቶች የፓርቲውን ራዕይና የወደፊት አሻራ ሁለንተናዊ እድገት ሰንቃችሁ፥ ተስፋ ተጋርታችሁ ማልዳችሁ ከአራቱም አቅጣጫዎች በመትመም ድጋፋቸውን በመግለጻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መንገዳችን መደመር፤ መዳረሻችን ብልፅግና ነው፤ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት አገር በማለት ከንቲባዋ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።