ቀጥታ፡

መንግስት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደው እርምጃ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭቱ የተሳለጠ እንዲሆን አስችሏል

አዳማ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የወሰደው እርምጃ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭቱ የተሳለጠ እንዲሆን ማስቻሉን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በመካከለኛው ምስራቅ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ፣ በተለይም በነዳጅ ምርት አቅርቦት ላይ ዓለምአቀፍ ችግር አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ ችግር በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም መንግሥት በአቅርቦትና ስርጭት ላይ አዲስ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል ጥረት አድርጓል።

በዚህም የነበረውን ዓለም አቀፍ ችግር በመቋቋም ማለፍ የተቻለ ሲሆን፣ አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች የተረጋጋ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል።

በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አሁናዊ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱ ምን እንደሚመስል ኢዜአ የሚመለከታቸውን አካላት፣ የነዳጅ ማደያዎችንና አሽከርካሪዎችን አነጋግሯል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጢሎ ዱግዳ፤ በነዳጅ አቅርቦት ላይ አጋጥሞ የነበረውን ችግር ለመቋቋም በከተማ አስተዳደሩ የነዳጅ ስርጭት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፣ የነዳጅ ስርጭቱ ፍትሃዊ እና ተደራሽ እንዲሆን መስራቱን አንስተዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በከተማዋ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ችግር የሌለ በመሆኑ ጥሩ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በከተማዋ በሚገኙ 19ኝ ማደያዎች በቂ የነዳጅ አቅርቦት መኖሩን ገልጸው፣ በዚህም ተገልጋዮች ካለምንም እንግልት እየተጠቀሙ መሆኑንና የእንቅስቃሴ ችግር አለመኖሩን አንስተዋል።

በከተማዋ ቀደም ሲል ህገወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመግታት በተደረገ ቁጥጥር 6ሺህ ሊትር ናፍጣና 6ሺህ ሊትር ቤንዚን መያዙን አስታውሰው፣ ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

በከተማዋ ከሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች መካከል የኖክ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ ግዛው አበበ እና የአፍሪካ ቁጥር 1 ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ ኮሚኒስት ወንድሙ፤ ቀደም ሲል በነዳጅ አቅርቦት ላይ የነበረው ችግር በመፈታቱ ደንበኞች በአግባቡ እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአሽከርካሪዎች መካከል ጌቱ ተስፋዬ እና አሸናፊ አለሙ፤ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የነበረበው ችግር በመፈታቱ አሁን ላይ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም