የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬትን ለመቁረጥ 90 ደቂቃዎች የቀራቸው ቀይ ቀበሮዎቹ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬትን ለመቁረጥ 90 ደቂቃዎች የቀራቸው ቀይ ቀበሮዎቹ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
16 ሀገራት በአራት ምድቦች ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ስምንት ሀገራት በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አልፈዋል።
በተጨማሪም ከየምድቡ ሶስተኛ የወጡ አራት ሀገራት የመለያ ጨዋታ አድርገው ቀሪ አላፊ ብሔራዊ ቡድኖች ይለያሉ።
በውድድሩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም በምድብ አንድ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ መለያ ጨዋታው ተሸጋግሯል።
ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ቱኒዚያን 1 ለ 0 መርታቱ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ቀይ ቀበሮዎቹ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ከሞዛምቢክ ጋር ዛሬ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በመሐመድ ስድስተኛ ኮምፕሌክስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድብ ሶስት ተደልድሎ ጨዋታውን ያደረገው የሞዛምቢክ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል።
የሞዛምቢክ ቡድን በመጨረሻ የምድብ ጨዋታው አንጎላን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለመለያ ጨዋታ ደርሷል።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሞዛምቢክን ማሸነፍ ከቻለ በኳታር አስተናጋጅነት ለሚከናወነው 20ኛው ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ያልፋል።
ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ካለፈ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።
ቀይ ቀበሮዎቹ ለጨዋታው የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።
አጥቂው ዳዊት ካሳው በውድድሩ ላይ በተመለከታቸው ሁለት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ላይ አይሰለፍም።
አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት ለኢትዮጵያ ህዝብ በእግር ኳስ ደስታ መስጠት እንፈልጋለን ሲሉ ገልጸዋል።
የቡድኑ ተጫዋቾችን ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ቁርጠኛ ናቸው፤ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን ብለዋል።
በሌላኛው የመለያ መርሐ ግብር ጋና ከዩጋንዳ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዘጋጇ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ኮትዲቯር፣ ካሜሮን፣ ታንዛንያ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል እና አልጄሪያ በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ ሀገራት ናቸው።
16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በአፍሪካ ዋንጫው እየተሳተፉ ካሉ 16 ሀገራት መካከል 10ሩ በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።
በዓለም ዋንጫው 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።