የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ በስኬት ጎዳና ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ በስኬት ጎዳና ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጽናት በማለፍ በስኬት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርሐ-ግብር አካሂዷል።
በማጠቃለያው መርሐ-ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ እንግዶች ታድመዋል።
የቦርድ ሰብሳቢው ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገሪቱን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ብርቅዬ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በሚሰጠው የላቀና ዘመናዊ አገልግሎት ምክንያት፣ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በየዘመኑ ከፍተኛ እውቅና እየተሰጠው እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
አየር መንገዱ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶች በጽናት በማለፍ ሁልጊዜም በስኬት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ከአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድነት ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ስትራቴጂ ቀርጾ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች አየር መንገዱ ስኬቶቹን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ተቋሙ ለበለጠና ለላቀ ስኬት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።