የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ አፍሪካውያንን ያስተሳሰረ የስኬትና የመቻል ዓርማ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ አፍሪካውያንን ያስተሳሰረ የስኬትና የመቻል ዓርማ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ አፍሪካውያንን ያስተሳሰረ የስኬትና የመቻል ዓርማ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርሐ-ግብር አካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በሺህ ዘመናት ታሪኳ ተቋማትን በመመሥረትና በማጽናት እምብዛም ሳይሳካላት መቆየቷን አስታውሰዋል።
በዘመናዊ ታሪክ ከገጠሟት ስብራቶች መካከል የተቋማት ስብራት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በፈተና ውስጥ ወጀቡን በማለፍ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ታሪክ እየሠሩ የተጓዙ ተቋማት እንዳሏትም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ አፍሪካውያንን ያስተሳሰረና ያኮራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ የስኬት ተምሳሌት እና የመቻል ዓርማ ነው ብለዋል።
የዘመናዊቱ አፍሪካ ታሪክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአፍሪካ ችግሮች ቀድሞ ደራሽ መሆኑንም አንስተዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ወቅት ለሰው ልጅ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን በዓለም ዙሪያ በማጓጓዝ የበኩሉን ማበርከቱንም አውስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለስኬት እንዲበቃ መሪዎቹና ሠራተኞቹ የከፈሉት ዋጋ በታሪክ የሚጠቀስ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ በመደገፍ፣ ሀገራችንን በአቪዬሽን መሠረተ ልማት ከፍ በማድረግ፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማገዝ፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት 80 ዓመታት ያስመዘገበው ዕድገት በተከታታይ ስኬቶች የታጀበ መሆኑን በማንሳት፤ ከጃን ሜዳ እስከ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰውን ዕድገትም አድንቀዋል።
ከኢትዮጵያውያን አልፎ መላው የጥቁር ሕዝብ በአየር መንገዳችን ይኮራል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አየር መንገዱ ለቀጣይ ስኬቱ በሚያደርገው ጉዞ መንግሥት መሪም ደጋፊም ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሰማንያ ዓመት የአቪዬሽን ታሪክ የሚዘክር ቋሚ ዐውደ ርዕይ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ዘመናዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሠረት ከጣሉ እና ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቀጣይም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ተቋሙ በትጋት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ በረራውን በ1938 ዓ.ም በአስመራ በኩል ወደ ካይሮ ማድረጉ ይታወሳል።