ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስደማሚ ስኬቶችን አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አስደማሚ ስኬቶች ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርሐ-ግብር አካሂዷል።

በየማጠቃለያ መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በማጠቃለያው መድረክ ላይ እንዳሉት፤ የምሥረታ በዓል መርሐ-ግብሩ "ዘመን ተሻጋሪ ስኬት" በሚል መሪ ኃሳብ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አየር መንገዱ ወደ ካይሮ "አንድ" ብሎ የጀመረው ታሪካዊ ጉዞ ዛሬ ላይ በአምስት አህጉራት 145 መዳረሻዎች እንዲኖሩት ማድረጉን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የ147 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን በማጓጓዝ በአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ ለመሆን መብቃቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡትን አስደማሚ ስኬቶች በቁጥር ሲያብራሩም፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የአዳዲስ አውሮፕላኖች ቁጥር በ47 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ የሚያጓጉዘው የደንበኞች ቁጥር በ97 በመቶ፣ ዓመታዊ ገቢው በ121 በመቶ ማደጉንና ትርፉም በሦስት እጥፍ መጨመሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማይናወጥ ጠንካራ መሠረት ላይ መገንባቱን ጠቁመው፤ በቀጣይም እነዚህን የስኬት እሴቶቹን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም