ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ዘገባ ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያን አጉልተው ማሳየት ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ዘገባ ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያን አጉልተው ማሳየት እንዳለባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለጹ፡፡

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለትና በድኅረ ምርጫ ወቅት ፍትሐዊ ሽፋን በመስጠት ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ ለመራጩ ሕዝብ ማድረስ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በድምፅ መስጫው ዕለት ሚዲያዎች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን መጠበቅ፣ መረጃን ከትክክለኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ብቻ መጠቀምና በቅንጅት ኢትዮጵያን ማጉላት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምታካሂደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለሀገራዊ ሕልውና እጅግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህ ምርጫ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒው ለተሰለፉ አካላት ትልቅና ግልጽ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በፍጥነትና በጥራት በመዘገብ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት በምርጫው ዕለትም በመድገም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የምርጫ ዴስክ ጸሐፊ ገናናው ለገሰ፤ ሚዲያው በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ትጋት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።


 

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አላዛር ታደለ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ አዎንታዊና ታሪካዊ አሻራ እንዲያኖር ሚዲያው ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በስፋት መሥራቱን ገልጸዋል።


 

በቀሪዎቹ ቀናትና በምርጫው ዕለትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ጋር በመቀናጀት ለጋራ ሀገራዊ ግብ እንደሚሠሩ አክለዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘላለም ገነሞ መራጩ ሕዝብ ይበጀኛል ያለውን አካል ይመርጥ ዘንድ ጣቢያው በሃምሳ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።


 

በቀጣይም በድምፅ መስጫው ዕለት መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች በፍጥነትና በፍትሐዊነት ተደራሽ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከፍተኛ አዘጋጅ ኤርሚያስ በጋሻው በበኩሉ፤ በቅድመ ምርጫው ወቅት ሲሠራ እንደነበረው ሁሉ በምርጫውና በድኅረ ምርጫው ወቅትም በትጋት መሥራት እንደሚገባ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም