ለአንጀት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች በውል ይታወቃሉ? ቀድሞስ መከላከል ይቻላል? - ኢዜአ አማርኛ
ለአንጀት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች በውል ይታወቃሉ? ቀድሞስ መከላከል ይቻላል?
እንደ ዘርፉ የሕክምና ባለሙያዎች ገለጻ፤ በአጠቃላይ የካንሰር ህመም ማለት የኅዋሶች (ሴሎች) ከተፈጥሯዊና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ መራባት ማለት ነው።
የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ቢንያም ተፈራ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከአንጀት ካንሰር ጋር በተያያዘ አጋላጭ ሁኔታዎቹንና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ አብራርተዋል።
መንስዔ (አጋላጭ ምክንያቶች)
እንደ ዶክተር ቢንያም ገለጻ፤ የአንጀት ካንሰር በዋናነት በትልቁ አንጀት ላይ የሚነሳ የካንሰር ዓይነት ነው።
የካንሰር ህመም መንስዔ በአብዛኛው ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ በአብዛኛው አጋላጭ ምክንቶችን ነው የምናነሳው ይላሉ። መፍትሔውም አንድ ወጥ እንዳልሆነና እንደ አጋላጭ ሁኔታዎቹ የሚሰጥ መሆኑን በማስገንዘብ።
የአንጀት ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ አጋላጭ ምክንያቶችም፤ ዕድሜ፣ ዘረመል እና የአኗኗር ዘይቤ በሚል በሦስት ተከፍለው እንደሚታዩ ያስረዳሉ።
ዕድሜ፡- ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የአንጀት ካንሰር የመከሰት ዕድል እየጨመረ እንደሚሄድ በመግለጽ፤ በተለይም ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን የመከሰት ዕድሉ እንደሚጨምር አመላክተዋል።
ዘረመል፡- የዘረመል ተጋላጭነት ከቤተሰብ የሚወረስ ወይም ከአካባቢ የሚገኝ አጋላጭ የዘረመል ለውጦች ካሉ ከ50 ዓመት ቀደም ብሎም ሊከሰት የሚችል የካንሰር ዓይነት ነው ይላሉ።
የአኗኗር ዘይቤ፡- በዋናነት የአንጀት ካንሰርን የሚያባብሱ ነገሮች ደግሞ የአኗኗር ዘይቤዎች መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።
በተለይም ከአመጋገብ አንጻር የፋይበር ይዘታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችን መመገብ፣ ቀይ ሥጋ እና በፋብሪካ የተቀነባበር (ፕሮሰስ የሆነ) ምግብ አብዝቶ መመገብ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያነሰው የአመጋገብ ዘዴና ሌሎችም ሊነሱ ይችላሉ ብለዋል።
በተጨማሪም አልኮል፣ ሲጋራ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ስፖርታዊ እንቅስቃሴ) አለማድረግ እና ተያያዥ ሁኔታዎች ለአንጀት ካንሰር ሊያጋልጡ እንደሚችሉ አንስተዋል።
ምልክቶች
የአንጀት የሥራ ሂደት መስተጓጎል፣ በአብዛኛው ቶሎ የማይሄድ ወይም እየተለዋወጠ የሚመጣ ድርቀት፣ ተቅማጥ፣ ደም የቀላቀለ ሰገራ መኖር፣ በሰገራ ወቅት የተለየ ማስማጥ፣ መንስዔው በውል ያልታወቀ ክብደት መቀነስ፣ መንስዔው ያልታወቀ ከፍተኛ ድካም የአንጀት ካንሰር ምልክቶች ከሚባሉት መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በርካቶች ምንም ዓይነት ምልክት ሳይታይባቸው በህመሙ ሊጠቁ እንደሚችሉም ባለሙያው ጠቁመዋል።
በአብዛኛው እነማንን ያጠቃል?
ዶክተር ቢንያም እንዳሉት፤ የአንጀት ካንሰር ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ በአብዛኛው በወንዶች ላይ ይከሰታል። በኢትዮጵያ ደግሞ ተቀራራቢ በሆነ ሁኔታ በሁለቱም ጾታዎች ላይ ይከሰታል።
በተለየ ሁኔታ የአንጀት ካንሰር ሊከሰትባቸው የሚችሉ ሰዎች የዘረመል አጋላጭ ምክንያቶች ያሉባቸው መሆናቸውንም አንስተዋል። በተለይም ከቤተሰብ የሚወረስ የዘር መለወጥ ያላቸው ሰዎች ከ50 ዓመት ቀደም ብሎ የአንጀት ካንሰር የመያዝ ዕድል እንዳላቸውም ይገልጻሉ።
የአሳሳቢነት ደረጃ
የአንጀት ካንሰር በሕጻናት ላይ አይከሰትም ማለት ባይቻልም አልፎ አልፎ በጣም ጥቂት የመከሰት ዕድል ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመው፤ በአጠቃላይ ግን የአንጀት ካንሰር ለሕጻናትና አዳጊዎች ያን ያህል በአስጊ ደረጃ እንደማይጠቀስ ያነሳሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡትና ማኅጸን ካንሰር በመቀጠል በ3ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በኢትዮጵያም ወንድንም ሴትንም ደምረን ካየነው በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል። ወንዶችን ለብቻ ነጥለን ካየነው ደግሞ 1ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የካንሰር ዓይነት ነው ያሉት ዶክተር ቢንያም፤ እስከ 6 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ካንሰር በየዓመቱ ይያዛሉ፤ ከ4ሺህ 500 የሚልቁት ደግሞ በየዓመቱ በዚሁ ካንሰር ይሞታሉ ሲሉ አብራርተዋል።
የሕክምና ሁኔታ
እንደ ዶክተር ቢንያም ገለጻ፤ የአንጀት ካንሰር በወቅቱ ሲደረስበት ታክሞ የመዳን ተስፋው በጣም ጥሩ ነው። ይህን የሚወስነው ግን በዋናነት በሽታው የተገኘበት ደረጃ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል። ስለዚህ ቶሎ የተገኘ የአንጀት ካንሰር እንደሚታከም ገልጸዋል። በተለይም በደረጃ 1 እና 2 ላይ የሚገኝ የካንሰር ዓይነት የመዳን ዕድሉ እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል።
ደረጃው እያደገ በሚሄድበት ጊዜ ግን ሕክምናውም እየተወሳሰበና አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚሄድ አንስተዋል። የመዳን ዕድሉም በዚያው መጠን እያስቸገረ መሄዱ አይቀርም ይላሉ።
አንጀት በጣም ረጅም በመሆኑ ሕክምናው ካንሰሩ እንደተገኘበት ደረጃ እና እንደተከሰተበት ቦታ እንደሚወሰንም አንስተዋል።
በአጠቃላይ ግን ላልተሠራጨ ካንሰር ቀዶጥገና (ኦፕሬሽን) ዋነኛ የሕክምና አማራጭ ነመሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪነት ኬሞቴራፒና የጨረር ሕክምና የሕክምናው አካል መሆናቸውን ገልጸዋል። በዋናነት ሦስቱ የሕክምና አማራጮች እንደሚሰጡ ገልጸው፤ እንደ ካንሰሩ ደረጃ የወሰን ሆኖ ሚኖ ቴራፒ እና ታርጌትድ ቴራፒ የሚባሉ ተጨማሪ የሕክምና አማራጮ ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።
ምክረ ሐሳብ
የአንጀት ካንሰርን ልንከላከለው የምንችለው የካንሰር ዓይነት ነው ብለዋል ዶክተር ቢንያም። በተለይም የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል፣ በመአጋገብ ሁኔታ ላይም በፋብሪካ የተቀነባበሩ (ፕሮሰስ የሆኑ) ምግቦችን (ቀይ ሥጋን ጨምሮ) አብዝቶ ባለመመገብ፣ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን አዘውትሮ በመመገብ፣ አትክልትና ፍራፍሬን በማዘውተር፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የአንጀት ካንሰርን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል።
በተለይም ማንኛውም ከ50 ዓመት በላይ የሆነው ሰው የአንጀት ካንሰር ምርመራ ቢያደርግ እንደሚመከርም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በቤተሰብ የአንጀት ካንሰር ተጠቂ ካለ ከ50 ዓመት በታች የሆኑም ምርመራ እንዲያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።