የከተሞች ትንሣኤ፡- የልማት አሻራ፣ የዕድገት እጥፋትና የነገው ብሩህ ተስፋ - ኢዜአ አማርኛ
የከተሞች ትንሣኤ፡- የልማት አሻራ፣ የዕድገት እጥፋትና የነገው ብሩህ ተስፋ
የከተማ ልማት ዕሳቤና ፖሊሲ የከተማውን ኅብረተሰብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመልስ ሥርዓት መገንባትን ቀዳሚ ያደረገ ነው። ከተሞችን ተስማሚ የመኖሪያ ሥፍራ ብቻ ሳይሆን አካታች፣ ስማርት እና ለኑሮ ምቹ የሆኑ የብልፅግና ማዕከላት የማድረግ ራዕይ ተይዟል። ዋነኛ ግቡም ከተሞችን የሁሉም ዜጎች የጋራ መኖሪያ ማድረግ፣ ፍትሓዊ የቤት አቅርቦትን ማረጋገጥ እና የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማዕከላት ማድረግ ነው።
መንግሥት “መደመርን” እንደ መንገድ በመውሰድ የከተሞችን ተግዳሮት ወደ ልማት ዕድሎች የመቀየር ስትራቴጂን ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም የገጠር-ከተማ ትሥሥርን በማጠናከርና የተሰባሰበ አሰፋፈር ያላቸውን ከተሞች በመፍጠር ለነገው ትውልድ የምትመች አገር የመገንባት ታላቅ ሥራ ተጀምሯል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ለዜጎች በተሻለ ቅልጥፍና እንዲቀርቡ የተደረገ ቢሆንም፣ ከተሞችን በተቀናጀ የረጅም ዘመን ፕላን የመምራት ውስንነት፣ የመረጃ አያያዝ ችግሮች እና ገቢን በሥርዓት አለመሰብሰብ አሁንም የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ተቋማዊ ሪፎርሞች በቁርጠኝነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተማ ልማት ዘርፍ ሞዴል ሥራዎች በፍጥነትና በጥራት ተከናውነዋል። ለአብነትም መዲናችን አዲስ አበባ በወንዝ ዳርቻ እና በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አማካይነት የአፍሪካ የከተማ ልማት ሞዴል እንድትሆን ተደርጋለች።
የጫካ ኢኮ-ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አረንጓዴ ኢኮኖሚንና ዘመናዊ መሠረተ ልማትን ያዋሐደ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ የጣና ዳርቻ፣ የጅማ የሥነ-ምኀዳርና የሐረር የኮሪደር ልማት ሥራዎች የመንግሥትን ሁለንተናዊ የለውጥ ዐቅም አሳይተዋል።
ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 206 ሺህ ሕገ ወጥ ይዞታዎች ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፣ ለ115 ሺህ ሰነድ-አልባ ይዞታዎች ሰነድ ተዘጋጅቷል። ባለፉት 5 ዓመታት በመንግሥት፣ በሪል ስቴት አልሚዎች እና በግል ቤት ሠሪዎች ትብብር ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ተገንብተዋል። በተጨማሪም ማኅበረሰብን በማስተባበር 166,207 የዐቅመ ደካማ ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል። ከደረጃ በታች የሆኑ የከተማ ቤቶች ድርሻም በ2013 ከነበረበት 75 በመቶ በ2017 ወደ 52 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በሚቀጥሉት ዓመታት የከተማ መሬትን ምርታማነት ለመጨመር የይዞታ ማረጋገጫ ሥርዓት የሚጎለብት ሲሆን፣ የመሬት አያያዝ እና አጠቃቀም ይበልጥ ፍትሓዊ እንዲሆን እቅድ ተይዟል ። በከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እና የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በትኩረት የሚሠራ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ዓመታት 2.2 ሚሊዮን ቤቶች እንዲገነቡ ይደረጋል።
በከተሞች ያለው የቤት ሽያጭ እና የቤት ኪራይ አሠራር ገበያ-መር ሆኖ ፍትሓዊ የገበያ ሥርዓትን እንዲከተል ማድረግ ያስፈልጋል ። ከተሞች ከበካይ ነገሮች የጸዱ እንዲሆኑ ከከተማ ይዞታ ውስጥ 30 በመቶው የአረንጓዴ ልማት ቦታ ሆኖ እንዲጠበቅ እየተሰራ ነው ። የመንገድ፣ የትራንስፓርት፣ የንጹሕ ውኃ እና የመብራት አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይገባል ።