ቀጥታ፡

በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 24/7 በመሥራት በዜጎች ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡና ማኅበረሰቡ ጤናማ በሆኑ አካባቢዎች አገልግሎት ማግኘት የሚችልባቸውን ፕሮጀክቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዓድዋ የገበያ ማዕከል እና የትራንስፖርት ተርሚናልን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡ 


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግሥት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በሚመጥን መልኩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል። 

ከተማ አስተዳደሩ ቃል በገባው መሠረት ዜጎች ምቹ በሆነ አካባቢ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያገኙባቸው በርካታ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን አንስተዋል። 

ለአብነትም ምቹ የእንቅስቃሴ መንገዶችን ማስፋፋት፣ ሕዝቡ በጥሩ ሁኔታ ላይ ሆኖ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያገኝባቸውን ተርሚናሎች መገንባት እንዲሁም ዘመናዊ የመሸጫ የንግድ ሱቆችን ማጠናከር ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በዛሬው ዕለትም የሕዝብን ክብር በሚመጥን መልኩ የተገነባው የዓድዋ የገበያ ማዕከልና የትራንስፖርት ተርሚናል መመረቁን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ይህም የተቀናጀ አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ ለመስጠት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀዋል። 

ከተማ አስተዳደሩ 24/7 በመሥራት በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ትጉህነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሀብተማርያም በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ የሚመጥኑና ለትውልድ አኩሪ የሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጸዋል። 

በዛሬው ዕለት ለንግድ እንቅስቃሴ መዘመንና ለትራፊክ ፍሰት መሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የዓድዋ የገበያ ማዕከል እና የትራንስፖርት ተርሚናል፤ ሌሊትና ቀን በመሥራት ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል። 

ይህ የዓድዋ የገበያ ማዕከል እና የትራንስፖርት ተርሚናል ፕሮጀክት በውስጡ በርካታ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን፣ የተለያዩ ምርቶች መሸጫ ሱቆችንና ሌሎችንም ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫዎችን እንደያዘ ጠቅሰዋል።


 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እየሠራ መሆኑንና የዛሬው ተርሚናል ምርቃትም የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም