ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የከተማ ልማት ሥራዎች ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ አድርገዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የከተማ ልማት ሥራዎች ከተሞችን ለነዋሪዎች የተመቹ፣ ለጎብኚዎች ደግሞ ውብና ሳቢ እንዲሆኑ ማስቻሉን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ገለጹ። 

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ረገድ በአፍሪካ ደረጃ አርአያነት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የከተማ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። 

ለከተሞች ልማት ትኩረት በመሰጠቱ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለጎብኚዎች ደግሞ ውብና ሳቢ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተተገበረው የኮሪደር ልማት፣ የከተሞችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹና ተስማሚ የአኗኗር ከባቢ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 

የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን የአፍሪካ ተምሳሌትና ለቱሪዝም ፍሰት ምቹ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ታላቅ የልማት ስኬት፣ የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚያረጋግጡ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን በስፋት ማካተት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ጥራት ያላቸው ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶችን በመገንባት ዜጎች በነፃነትና በደኅንነት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለ ሲሆን፣ ለተሽከርካሪዎችም ምቹና ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች በመስራት የትራፊክ ፍሰቱ በእጅጉ እንዲቃለል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የአካባቢ ጥበቃን፣ የአረንጓዴ ልማትንና የነዋሪዎችን ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ 

ይህ ሁለንተናዊ የከተማ ልማት ሥራ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በማሻሻል ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ 

መንግሥት ለከተሞች በሰጠው ትኩረት ለውጥ ከተመዘገበባቸው የልማት ሥራዎች አንዱ የሆነው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን ሕይወት በተግባር መቀየሩን ተናግረዋል።  

መርሃ ግብሩ በሰማንያ ስምንት ከተሞች የሚተገበርና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተጠቃሚዎቹ መካከል 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚበልጡት ተመርቀው ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሚሸጋገሩ አብራርተዋል። 

ይህ አሠራር ዜጎች በኢንተርፕራይዝ ደረጃ በመደራጀት ራሳቸውን ከመደገፍ ባለፈ፣ ለሌሎችም ተጨማሪ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ስኬታማነት በአፍሪካ ደረጃ ሞዴል የሆነና ሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ እየወሰዱበት ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም