የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና እየሰጠ ነው
ጎንደር ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የልብ ህክምና ማግኘት ላልቻሉ ወገኖች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሆስፒታሉ ከግንቦት 13 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም እየሰጠ በሚገኘው ህክምና ለ14 ህጻናት ህክምናውን መስጠት መቻሉም ተገልጿል።
በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ትምህርትና ህክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ ደምስ ሙላቱ እንደተናገሩት፤ በአመት እስከ 500 የሚደርሱ የልብ ጤና ችግር ያለባቸው ህጻናት ለህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ።
የህጻናቱ ቤተሰቦች የልብ ህክምናውን ለማግኘት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ከፍለው የማሳከም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ችግር ለማቃለልም ከጣሊያን ሀገር ከመጡ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የህክምና ባለሙያዎቹ፣ በአፈጣጠር ምክንያት የልብ ጤና ችግር ለገጠማቸውና እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ህክምናውን እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህክምናው የህጻናቱን ጤና ከመመለስ ባሻገር በቴክኖሎጂና በእውቀት ሽግግር ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑንና ይህም ሆስፒታሉ በቀጣይ ራሱን ችሎ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ ደምስ ጠቁመዋል።
የልኡካን ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ተድላ በበኩላቸው፤ የህክምና ቡድኑ በኢትዮጵያ በሚኖረው የ45 ቀናት ቆይታ በጎንደር፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ለ175 ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ለመስጠት ማቀዱን ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እስከ 24 ለሚደርሱ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና ለመስጠት እቅድ ተይዞ፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ለ14 ህጻናት ህክምናውን መስጠት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ከጤና ሚኒስቴር ጋር በተደረሰ ስምምነትና በአጋር የጤና ተቋማት ድጋፍ እየተሰጠ የሚገኘው ይህ ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና በክፍያ ቢሆን ኖሮ፣ ለአንድ ህጻን የህክምና ወጪ ብቻ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ይጠይቅ እንደነበር አስታውቀዋል።
ይህ የነጻ የልብ ቀዶ ህክምና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ልጆቻቸውን ከፍለው ማሳከም ሳይችሉ ለቆዩ ወላጆች ትልቅ እፎይታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ናቸው፡፡
ሰብአዊነትን በመላበስ አህጉር አቆራርጦ በመምጣት ህክምናውን እየሰጠ ለሚገኘው የልኡካን ቡድን ምስጋና በማቅረብ፣ የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀውን የባህል አልባሳትና ወካይ ቅርሶች በስጦታ አበርክተዋል፡፡
በጎንደርና በአካባቢው የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ተቋም ባለመኖሩ ልጃቸውን ማሳከም ሳይችሉ ቆይተው እንደነበር የጠቀሱት ደግሞ ለ9 ወር ልጃቸው ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ያገኙት ወይዘሮ ሀረገወይን ደሴ ናቸው።
በገንዘብ ማጣት የልጃቸውን ህመምና ስቃይ ከመመልከት የታደጋቸው ይህ የነጻ ህክምና አገልግሎት ለሌሎችም ችግረኛ ወገኖች እንዲደርስ ጠይቀዋል።