ቀጥታ፡

በፓርኩ ያለው የተሟላ መሰረተ ልማትና በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ ባለሀብቱን መሳብ እያስቻለ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው የተሟላ መሰረተ ልማትና በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ አልሚ ባለሀብቶችን እየሳበ መሆኑ ተገለጸ።

በፓርኩ የአዳዲስ ፋብሪካዎች ምረቃና የዕውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ሙዝና ቡናን በዘመናዊ መልኩ ዕሴት ጨምረው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ሁለት አዳዲስ ፋብሪካዎች በይፋ ሥራ ጀምረዋል።


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊና የፓርኩ የቦርድ ሰብሳቢ መምሩ ሞኬ፤ የኢኮኖሚው መሰረት የሆነውን የግብርና ምርት ዕሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ በኩል የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለበርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላለት ፓርኩ ለባለሀብቶች ምቹ መሆኑ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።


 

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኃይሉ የተራ፤ ፓርኩ ሥራ ከጀመረባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በተኪ ምርት፣ በገበያ ትስስርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።

በፓርኩ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሰማራት ዛሬ ሥራ የጀመሩትን ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ኩባንያዎች በምርት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በዚህም እስካሁን ከ26ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ፓርኩ ባለው የመሰረተ ልማት ምቹነት፣ በመንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ታክሎበት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ በይፋ ሥራ ከጀመሩት ፋብሪካዎች መካከል የኤፔክስ ማኑፋክቸሪንግና ትሬዲንግ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ መስፍን ተፈራ ኩባንያቸው ሙዝን በዘመናዊ መንገድ በችፕስ መልክ ለገበያ ለማቅረብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

የፋብሪካው ሥራ መጀመር በክልሉና በአጎራባች አካባቢዎች በስፋት በሙዝ አምራችነት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጨማሪና አስተማማኝ ገቢ ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ከ60ሺህ ከሚሆኑ አምራቾች ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩን አመልክተዋል።

ኩባንያው ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ወደ ውጭ እንደሚልክም ገልጸዋል።


 

ሌላው በቡና ማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማራው የቻይናው 'መይመይ ኮፊ ፕሮሰሲንግ' ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ጄ ሶን፤ በፓርኩ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታና መሰረተ ልማት ተስበው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካው ቡናን ከአርሶ አደሩ ማሳ ቀጥታ በመረከብ፤ ማጠብና መፍጨት ጀምሮ የተጠናቀቀ ዝግጁ ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ እስከማቅረብ ድረስ ያለውን ሙሉ ሂደት እዚያው ፓርኩ ውስጥ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

 

በዕለቱ ዕውቅና ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል የ'ጎልደን' የአቮካዶ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት ወይዘሮ ይርጋለም አስፋው ፋብሪካው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 16 ኮንቴይነር የአቮካዶ ዘይት ምርት ወደ ውጭ ሀገር መላክ ችሏል ብለዋል።

ዛሬ የተሰጣቸው ዕውቅና በቀጣይ ይበልጥ ጠንክረው እንዲሰሩ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም