በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው የላቀ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው የላቀ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው የላቀ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያና ፓስፊክ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አምኃ ኃይለጊዮርጊስ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ያለመው የዱባይ-ኢትዮጵያ ቢዝነስ ትስስር ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያና ፓስፊክ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አምኃ ኃይለጊዮርጊስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዱባይ-ኢትዮጵያ ቢዝነስ ትስስር ፎረም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ያላቸው ሁለንተናዊ ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸው፤ ፎረሙ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ስትራቴጂያዊ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት ያሉት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አምኃ፤ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ወሳኝ አጋር መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ መዳረሻ መሆኗን ገልጸው፤ 169 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2018 ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት በጥልቀትና በስፋት እያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ትብብሩም የሁለቱ ሀገራት የጋራ ብልጽግናን እውን ሊያደርግ በሚችል የጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብዝኃና እምቅ የንግድና ኢንቨስትመንት አቅም፣ ለኢንቨስትመንት የተመቹ አሠራሮች እንዳሏት በማንሳት፤ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች ዕድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ራሼድ አብዱላ አልሸሂ፤ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የምትከተለው የዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትስስር ሞዴል ኢትዮጵያንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የገበያ አማራጭና እየተገበረች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጥቀስ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረች መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በታዳሽ ኃይል፣ በግብርናና ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የምታጠናክርበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜሳ በበኩላቸው፤ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ለምክር ቤቱ አባል ኩባንያዎች ዋነኛ መዳረሻና መገኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የዱባይ ኩባንያዎች በዲጂታል አገልግሎት፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ ለሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎች ትብብር መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባና የዱባይ የቢዝነስ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በጋራ በመሰማራት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡