ቀጥታ፡

በክልሉ በለውጡ ዓመታት ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል

ሸገር፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ገለጹ።

በሸገር ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጬና በገላን ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የ“ቡኡራ ቦሩ” ቅድመ መደበኛ እና የአንደኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም የሕዝብ መናፈሻ ፓርኮች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።


 

በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች የመለሱ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት በመገንባታቸው የሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ችሏል። 

በተለይም በእውቀትና ቴክኖሎጂ የዳበረ፣ አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።

በሸገር ከተማ በኮዬ ፈጬና ገላን ክፍለ ከተሞች ዛሬ የተመረቁት ትምህርት ቤቶች፣ የመጠጥ ውኃና የፓርክ ፕሮጀክቶች የዚሁ ሰፊ እንቅስቃሴ ማሳያ መሆናቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፤ መምህራን ትውልዱን በማነጽ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን በመሆን ሁለንተናዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ በሸገር ከተማ ባለፉት ሦስት ዓመታት የከተማዋን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል። 


 

በከተማዋ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሕብረተሰቡ የልማት ጥያቄ በተሟላ መልኩ እየተመለሰ መሆኑንም አክለዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በከተማዋ መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት፣ የከተማዋን ገቢ ከማሳደግ፣ የጤና ተቋማትን ከመገንባትና ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አኳያ ተጨባጭ ሥራዎች መከናወናቸውን ከንቲባው አንስተዋል። 

በተለይም የከተማዋን አርሶ አደር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቀው ለአርሶ አደሮቹ መተላለፋቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከተማ አስተዳደሩ 448 የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለመገንባት አቅዶ እስካሁን 338 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ሳይመሠረት በፊት በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ100 ሺህ የማይበልጥ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከ400 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን ከንቲባው ገልጸዋል። 

በተጨማሪም በገላን ክፍለ ከተማ ተገንብቶ የተመረቀው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከ33 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።


 

የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኩመላ ሂርጳ፤ በክፍለ ከተማው በበጀት ዓመቱ የታቀዱ 25 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመንግሥት በጀትና በሕዝብ ተሳትፎ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ዛሬ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት ትምህርት ቤቶች በክፍለ ከተማው ከተከናወኑት ስኬታማ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቶቹ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆቹን በአቅራቢያው ለማስተማር እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም