በምዕራብ ሸዋ ዞን የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አምቦ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ስራዎች በጥራትና በብዛት እየተገነቡ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
በዞኑ ኤጀሬና ወልመራ ወረዳዎች የተገነቡ የኮሪደር ልማት፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንፃ እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታን ጨምሮ የዞኑና የወረዳዎቹ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ዲዳ ጉደታ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ይገኛል።
በዞኑም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለረጅም ጊዜ የህብረተሰቡ ጥያቄ ሆነው የቆዩትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የሌሎች ዘርፎች ጥያቄዎችን መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።
ወደፊትም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ስራዎች በጥራትና በብዛት የመገንባቱ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።
የኤጄሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዱኛ ብሩ በበኩላቸው፤ በወረዳው ለአገልግሎት ከበቁ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የሁለት ኪሎ ሜትር የከተማ ኮሪደር ልማት፣ የወተት ላሞች እርባታና የከብት ማደለቢያ ማዕከላት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
በወረዳው ዛሬ ለምርቃት የበቁት እነዚህ ፕሮጀክቶች በህብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግሥት በጀት በአጠቃላይ 122 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የወልመራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጋሪ በበኩላቸው፤ አካባቢው የበጋ ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል እህሎች በስፋት የሚመረቱበት መሆኑን ገልጸው፤ ዛሬ የተመረቀው የ13 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ወረዳውን ከቀበሌዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው አስረድተዋል።
ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የከብትና የዶሮ እርባታ ማዕከላት፣ ባለ ሶስት ወለል የወረዳ ፍርድ ቤት ህንፃ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ ክፍሎች ይገኙበታል ብለዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግሥት በጀትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በአጠቃላይ 250 ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ስሪኔሳ ኩማላ፤ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ባለ ሶስት ወለል የፍርድ ቤት ህንጻ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የህግ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የኤጀሬ እና የወልመራ ወረዳ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የልማት ጥያቄዎቻቸው ለብዙ ዓመታት መልስ ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ለተገነቡላቸው ፕሮጀክቶች የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።