ቀጥታ፡

መንግስት ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ተግባራትን አከናውኗል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህርዳር፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል መንግስት ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ተግባራትን አከናውኗል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።

"ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የለውጡ መንግስት ፕሮጀክቶችን በማቀድና ፈጥኖ በመጨረስ ለሀገሪቱ አዲስ ልምምድ አበርክቷል።

በቱሪዝም፣ በማዕድን ፣ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶችም ለአገር እድገት መሰረት የሆኑና የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም መላውን ህዝብ በማሳተፍ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤት እያስገኘ በመምጣቱ ለልማት ስራው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

በቀጣይም ህዝቡን በማስተባበር በልማትና በሰላም ማስፈን ስራዎች ለማረባረብ እንደሚሰራ ጠቁመው ምርጫውን በሰላም ለማጠናቀቅ ህዝቡ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ‎‎‎አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ ሀገር ጸንታ የምትቀጥለውና የምትሻገረው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በንግግርና በውይይት መፍታት ሲቻል ነው ብለዋል።


 

የሚገጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በመግባባት መፍትሔ በመስጠት የሚካሄዱ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

‎ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ህብረተሰብ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

‎ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና የባህር ዳር ከተማን ተመራጭ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመድረኩም የክልሉና የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም