ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ስፍራዎች ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ ጥንካሬ ይኖራቸዋል። 

ከእርጥበት አዘል የአየር ሁኔታው ጋር ተያይዞም የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ገልጿል።

በዚህም በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ በምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር አመልክቷል።

በሚቀጥሉት ቀናት ከሚኖሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት፤ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።

አልፎ አልፎ በውኃ አካላትና በአካባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት፤ በጥቂት የደቡብ፣ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች መጠቆማቸውን ገልጿል።

ይህም ለግብርና ሥራ በቂ የአፈር ውስጥ እርጥበት እንዲኖር በማድረግ ለሰብሎች፣ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አስታውቋል። 

ከተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የውኃ ማጠራቀሚያዎችን አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ለቋሚ ተክሎችም አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጿል።

በተጨማሪም ለመኸር ሰብሎች የማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራት፣ ፍሬ በማፍራትና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት፣ ለአረንጓዴ ዕፅዋት ልምላሜ፣ ለመጠጥ ውኃና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት መሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቁሟል።

በተፋሰሶች ላይ ያለውን የእርጥበት ሁኔታ በተመለከተም ባሮ አኮቦ፣ መካከለኛና ታችኛው አባይ፣ በአብዛኛው ኦሞ ጊቤ፣ በላይኛውና መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የገጸ ምድር ውኃ ፍሰት ይኖራቸዋል ብሏል። 

በላይኛው ገናሌ ዳዋ፣ ኦጋዴን፣ ታችኛው ተከዜ እንዲሁም በላይኛውና መካከለኛው ዋቤ ሸበሌ ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር ውኃ ፍሰት እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብሏል።

በተጨማሪም ደረቅ የገጸ ምድር ውኃ ፍሰት የሚኖራቸው በአብዛኛው አፋር ደናኪል፣ አይሻ፣ መካከለኛና ታችኛው አዋሽ እንዲሁም በታችኛው ገናሌ ዳዋ መሆኑን የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ሲል ገልጿል።

በሌላ በኩል በበልግ ወቅት የሚኖረው የሙቀት መጠን መጨመርና በሌሊት ደግሞ የሚታየው ወበቅ አንዱ የዚህ ወቅት ክስተት መሆኑን ጠቁሟል። 

ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ጋር ተያይዞም በተለይም በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ32 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም