በአፋር ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ሰመራ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑር ገለጹ።
በክልሉ ቂልበቲ ራሱ ዞን ኮነባ ወረዳ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመር ኑር በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በልዩ ትኩረት እያከናወነ ይገኛል።
ለአብነትም ቀደም ሲል ግንባታቸው ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በቅንጅት በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ መመለስ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ የተጀመረው ስራ የበለጠ የሚጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ በበኩላቸው፤ የንፁህ መጠጥ ውሃን በአርብቶ አደር አካባቢዎች ለማድረስ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን የተመረቁት ፕሮጀክቶችም ቢሮው ከ'ዋን ዋሽ' ፕሮግራም ጋር በመተባበር የገነባቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በኮነባና አካባቢው የሚኖሩ ከ25 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በዞኑ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን በማሳደግ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ መሰራቱን የገለጹት ደግሞ የቂልበቲ ራሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ዓሊ አስሃብ ናቸው።
የፕሮጀክቶቹ እውን መሆን በተለይም የእናቶችን እንግልት በማስቀረት፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ እንዲያውሉ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የኮነባ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ያሲን በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በአካባቢው የንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ህብረተሰቡ ይቸገር እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለሱን አክለዋል።
በዚህ የፕሮጀክቶች ምረቃ መርሃ ግብር ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴንን ጨምሮ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።