በዞኑ ለመኸር ወቅት የተዘጋጀ ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለመኸር ወቅት የተዘጋጀ ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው
ደብረ ብርሃን ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለመኸር ወቅት እርሻ ለምርት ማሳደጊያነት በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትንና እርጥበትን በመጨመር ለምርት እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በዚህም በዞኑ ለ2018/19 ምርት ዘመን መኸር ወቅት በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ከ363ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
እስካሁንም ሰባት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማሳን ደጋግሞ በማረስ ከአፈር ጋር በመቀላቀል ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከልም አቶ ኩራ ተሾመ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘጋጅተው በመጠቀማቸው የማሳቸው ለምነት መጨመሩ የሰብል ምርታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በቢራ ገብስ፣ በአተርና ባቄላ ዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ገበየሁ ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ ባለፉት አመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በመጠቀማቸው ምርታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለፋብሪካ ማዳበሪያ ግዥ የሚያወጡትን ወጭ መቀነስ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ዘንድሮም ለመኸር ወቅት እርሻ የሚሆናቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከቅጠላቅጠል፣ ከእንስሳትና ሰብል ተረፈ ምርት በማዘጋጀት ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች በዘር የመሸፈን ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ በ2018/19 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከ563 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል በማልማት 20 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።