ቀጥታ፡

የመዲናዋ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ-ልማቶች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለቱሪዝም ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ-ልማቶች ተተኪዎችን ለማፍራትና ለቱሪዝም ዕድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ጥራት ያላቸውና ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟሉ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

ኢዜአ ያነጋገረው ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ሰይድ ኪያር፤ እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ለወጣቶች አዲስ ተስፋና ዕድል ይዘው የመጡ ናቸው ብሏል፡፡

እነዚህ በዘመናዊ መልክ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በከተማዋ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ እና የወጣቱን ትውልድ ሁለንተናዊ አቅም የሚገነቡ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡


 

ቀደም ሲል በመዲናዋ የነበሩት የስፖርት ማዘውተሪያዎች በቁጥር አነስተኛና ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው፣ ዘርፉ በተገቢው መንገድ እንዳያድግ ትልቅ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ጠቅሷል።

ይህም ወጣቶችን ከስፖርት ከማራቁ ባሻገር፣ ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን በሀገር ደረጃ ለማፍራት ትልቅ ማነቆ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ የዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟሉና ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ የስፖርት ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው፤ ለተተኪ ስፖርተኞች ትልቅ ብስራት ይዞ መምጣቱን አብራርቷል፡፡

ሀገሪቱ በስፖርቱ ዘርፍ የነበራትን ታላቅ ስም ለመመለስና ብቁ ስፖርተኞችን በስፋት ለማፍራት የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ገልጿል፡፡

እነዚህ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ተተኪ ስፖርተኞችን በስፋት ለማፍራትና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ነው የጠቀሰው፡፡


 

አዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት ከዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ባሻገር፣ ወደ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ማዕከልነት እያደገች የመጣች ከተማ መሆኗን እንዲሁ፡፡

በመዲናዋ በስፋትና በጥራት የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ተመራጭ እንድትሆን እንዳስቻላት ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራትና ጤናማ ማህበረሰብን ከመገንባት ባለፈ፣ ለስፖርት ቱሪዝም ማደግ አይነተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ልማትና ማኔጅመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉንና ስፖርቱን በቅንጅት ያስተሳሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም