በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ከ246 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ ተኪ ምርት ማምረት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ከ246 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ ተኪ ምርት ማምረት ተችሏል
ባህርዳር፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፍ ከ246 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶች መመረታቸውን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ የማዕድን ሃብትን በማልማት ለሀገር እድገትና ብልጽግና ለማዋል እየተሰራ ነው።
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዝናው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት በጥናት በመለየት በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ እየለማ ይገኛል።
በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማሳተፍ በተያዘው ዓመት 18 የማዕድን ሃብት የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ርክክብ መፈፀሙን ገልፀዋል።
በዚሁ መሰረትም የኮንስትራክሽን፣ ብረትና ብረት ነክ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ ለኃይል አቅርቦትና መሰል አገልግሎት የሚውሉ ማዕድናት በክልሉ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የጥናቱን ግኝት ለባለሃብቶች በማቅረብ ወደ ልማት እንዲገቡ በተደረገው ጥረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 169 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚህም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን በላይ ጅብሰም፣ ላይም ስቶን፣ ሲልካሲድ፣ ድንጋይ ከሰል፣ እምነ በረድ፣ ግራናይትና መሰል ምርቶችን በማምረት ከ246 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከ18 ሺህ 500 ኪሎ ግራም በላይ እሴት የተጨመረበትና ጥሬ ኦፓልና ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ከ13 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻሉን አስረድተዋል።
በዘርፉ በተደረገ እንቅስቃሴም ለ33 ሺህ ወገኖች የስራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንዳስቻለም ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ በተለይም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ግብዓት ሙሉ በሙሉ መሸፈን እንዳስቻለ ጠቅሰው፤ ይህም በከተሞች እያደገ የመጣውን የግንባታ እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ማገዙን አረጋግጠዋል።
በክልሉ 25 በመቶ የሚሸፍን የስነ ምድር ካርታ ጥናት የተካሄደ ሲሆን የ51 ማዕድናት የስርጭት የቦታ ልየታ ስራ መከናወኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።