ቀጥታ፡

ማይክል ካሪክ የማንቸስተር ዩናይትድ ቋሚ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ማንቸስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተጫዋቹን ማይክል ካሪክን የሁለት ዓመት ውል በመስጠት የክለቡ ቋሚ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አስታወቀ።

የ44 ዓመቱ ማይክል ካሪክ ክለቡን በቋሚነት እንዲመራ የተመረጠው፣ የቀድሞው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ጥር ወር ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸውን ተከትሎ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት በነበረው አጭር ቆይታ ያስመዘገበውን መልካም ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ካሪክ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ባሳየው ተከታታይ የውጤት መሻሻል ክለቡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ የሚችልበትን ደረጃ ማረጋገጥ መቻሉን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው እሁድ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ያደረገውን ጨዋታ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፉን ተከትሎ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።

አሰልጣኙ ቡድኑን በጊዜያዊነት መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች መካከል በ11ዱ ድል ቀንቶታል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ካሪክ በጥር 13 ቀን 2026 (እ.ኤ.አ) ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ 36 ነጥቦችን የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም በሊጉ ካሉ ክለቦች ሁሉ በወቅቱ ከፍተኛው የተሰበሰበ ነጥብ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህንን ተከትሎም ካሪክ ለፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሽልማት ከታጩት ስድስት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

ማይክል ካሪክ ሹመቱን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፣ ከ20 ዓመታት በፊት ወደ ኦልድ ትራፎርድ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የክለቡን ታላቅነት እንደሚረዳ ገልጾ፣ ይህንን ልዩ ክለብ በቋሚነት የመምራት ኃላፊነት በመስጠቱ ታላቅ ኩራት እንደተሰማው ተናግሯል።

ባለፉት አምስት ወራት የተጫዋቾች ስብስብ ያሳየው የአንድነትና የጽናት መንፈስ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሶ፣ ወደፊት ክለቡን ወደ ቀድሞ ታላቅነቱ ለመመለስና ለትላልቅ ዋንጫዎች ለመፎካከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቋል።

የቀድሞው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በክለቡ በነበራቸው የ14 ወራት ቆይታ ማብቂያ ላይ በተመዘገቡ ደካማ ውጤቶች እና በታክቲክ ምርጫዎች ዙሪያ ከክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበራቸው አለመግባባት ሳቢያ ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸው ይታወሳል።

ማይክል ካሪክ እ.ኤ.አ በ2021 የቀድሞው አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሻየር ከተሰናበቱ በኋላም ቡድኑን ለሦስት ጨዋታዎች በጊዜያዊነት መምራቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ቆይታው በሜዳ ላይና ከሜዳ ውጪ ባሳየው አመራር የክለቡን ባለሥልጣናትና ደጋፊዎች አድናቆት አትርፏል።

አዲሱ ቋሚ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በማንቸስተር ዩናይትድ በነበረው የ12 ዓመታት የተጫዋችነት ዘመን አምስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ ማሸነፍ የቻለ የክለቡ ስኬታማ ተጫዋች እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው አውስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም