የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስምንት አስርት ዓመታት ወርቃማ ስምና ዝና የአፍሪካ የትስስር ተምሳሌት እንዲሆን አስችሎታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስምንት አስርት ዓመታት ወርቃማ ስምና ዝና የአፍሪካ የትስስር ተምሳሌት እንዲሆን አስችሎታል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስምንት አስርት ዓመታት ወርቃማ ስምና ዝና ጉዞ የአፍሪካ የትስስር ተምሳሌት እንዲሆን ማስቻሉን እንግሊዛዊ ዲፕሎማት ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ''አዲሱ የአፍሪካ መንፈስ” የሚለው ሃሳብ የአህጉሪቱን የዕድገትና ብልፅግና ጉዞ በማፋጠን አፍሪካን ከቀሪው ዓለም የሚያገናኝበት መገለጫው እንዲሆን አድርጎታል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የኮሙኒኬሽንና የሶፍት ፓወር ክፍል ኃላፊ ጄሚ ማንዝብሪጅ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መለያ ዕሴት የገነባ ተቋም ነው።
የአየር መንገዱ ዘመናዊ አውሮፕላኖችና የበረራ ምልክት የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት አፍሪካን ከቀሪው ዓለም የሚያገናኝበትን ዕድል እንደፈጠረለት ገልጸዋል።
አፍሪካን ከቀሪው ዓለም በማገናኘት የሚሰጠው አስደናቂ የበረራ አገልግሎት ከሌሎች አየር መንገዶች ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የበረራ ተደራሽነቱ የአየር መንገዱን አውሮፕላኖች መለያ ምልክት በማጉላት ተምሳሌታዊ አገልግሎት የሚሰጥበትን ዕድል እንደፈጠረ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስምንት አስርት ዓመታት በገነባው ወርቃማ ስም አፍሪካን ከዓለም በማገናኘት ቁልፍ ሚና እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም የዓለም ማህበረሰብ የአፍሪካን የቱሪዝም፣ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሪ ተዋናይነቱን የሚያጎለብትበትን የዕውቀትና ልምድ ልውውጥ ማዕከል እንዲሆን ማስቻሉንም ገልጸዋል።
የአየር መንገዱ ምቹ የበረራ መስተንግዶ ደንበኞች የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የመስህብ መዳረሻ የሚጎበኙበትን ዕድል እንደፈጠረ ጨምረው ተናግረዋል።