በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል
ዲላ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተደራሽነት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ የ140 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ የውል ስምምነት መርሃ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለመጪው ዓመት ለትምህርት አገልግሎት ለማብቃት ርብርብ ይደረጋል ተብሏል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በ"ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ ህብረተሰቡን በማስተባበር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና አዲስ ግንባታ ሥራ ውጤት አስገኝቷል።
ይህም የመማር ማስተማር ስራውን በማቀላጠፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸው የዚሁ አካል የሆነው የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የዛሬው 140 የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ በማድረግ ትውልድ የማነጽ ተግባርን ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተሳትፎና ተደራሽነትን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ ናቸው።
በክልሉ የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ 140 የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለቀጣይ ዓመት የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ይህም የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማስጠበቅ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ያለውን ድርሻ እንደሚያጎላው ነው የገለጹት።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሕጻናት በምቹ አካባቢ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሚገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችም በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል።