የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሩን እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሩን እያጠናከረ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር እያጠናከረ መምጣቱን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በዱባይ የንግድ ምክር ቤት የተዘጋጀው የዱባይ - ኢትዮጵያ ቢዝነስ ትብብር ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ምቹ የኢንቨስትመንት ሥነ-ምህዳርና የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ያላት ስትራቴጂያዊ የቢዝነስ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የወጣቶች ምድር፣ የአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን አፍሪካውያን የገበያ መዳረሻ እንዲሁም የብቁ የሰው ኃይል መገኛ ናት ብለዋል፡፡
ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለንግድና ኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆኑ አሠራሮችን በማስወገድ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተሟላ መሠረተ ልማት ፈጣንና ቀልጣፋ የንግድ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ግዙፉን አየር መንገድ እየገነባች መሆኑን በማንሳት፤ የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን በማሳለጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው ሥራ እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ሁለንተናዊ ስትራቴጂያዊ ትብብር እያደገ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር)፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ትብብሩ በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ አድርገዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሁለንተናዊ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ አቅም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አጋዥ መሣሪያ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
መንግሥት ለንግድና ኢንቨስትመንት ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ፤ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
የዱባይ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አሊ ራሼድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወሳኝ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የገበያ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በወሳኝ ስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድር እና በአፍሪካ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር እያደገ መምጣቱን በመጥቀስ፤ የዱባይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን መዳረሻቸው እያደረጓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ አንድ ሺህ 676 በሥራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በዱባይ ንግድ ምክር ቤት አባልነት ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በንግድ፣ ሪል-ስቴት፣ ሎጂስቲክስና መሰል ዘርፎች መሰማራታቸውን በመጥቀስ፤ በኢትዮጵያ እና ዱባይ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አይናለም አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የግሉን ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንት እያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ትብብር ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሪፎርም የወጪ ንግድን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ትብብርን አሳድጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የዱባይና የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በትብብር በመሥራት በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡