ቀጥታ፡

ታዋቂው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ ዲላን ፔጅ ሐረርን ለመጎብኘት መዘጋጀቱ ታሪካዊቷን ከተማ ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ነው

ሀረር፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ታዋቂው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ ዲላን ፔጅ ሐረርን ለመጎብኘት መዘጋጀቱ ታሪካዊቷን ከተማ ለዓለም ይበልጥ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የሀረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም ቅርስ ቢሮ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ የታሪክና የባህል እሴቶችን ለአለም ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ዲላን ፔጅ በአዲስ አበባ ብኝት በማድረግ ጀምሯል።

በመቀጠልም ወደ ታሪካዊቷ እና ውቧ ሐረር ከተማ በመጓዝ ጉብኝት ለማድረግ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

ከዓለም ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ የሆነው እንግሊዛዊው ዲላን ፔጅ በሀረር በሚኖረው ጉብኝት በተለይም "ጅቦችን ለመመገብ ጓጉቻለሁ” ብሏል።


 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ ተወለዳ አብዶሽ፤ ሐረር የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቀልብ ይበልጥ እየገዛች መጥታለች ሲሉ ተናግረዋል።

ሐረር ከተማ የኮሪደር ልማቱ ካጎናጸፋት ውበት ጋር ተዳምሮ እጅግ ማራኪ ከተማ መሆኗን አንስተው፤ በዚህም ይበልጥ የጎብኝዎችን ትኩረት እያገኘች ነው ብለዋል።

በመሆኑም ታዋቂው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ ዲላን ፔጅ ሐረርን ለመጎብኘት መዘጋጀቱ ታሪካዊቷን ከተማ ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በቆይታው በከተማዋ ተዘዋውሮ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኝ መሆኑን እንዲሁም ብዙዎች ለመመልከት የሚጓጉለትን ጅብ የመመገብ ትርዒት የሚመለከት መሆኑን አንስተው፤ በመልካም መስተንግዶ እንቀበለዋለን ብለዋል።

ከ19 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ተጽእኖ ፈጣሪው ዲላን ፔጅ ጉብኝት ዓለም ቅርስ የሆነውን ጁጎልን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች መስህቦችን ለዓለም ይበልጥ ለማስተዋወቅ ጥሩ እድል ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም