ቀጥታ፡

የአካባቢ ፀጋን በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

እንሴኖ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ ውጤታማ ያደረገው የአካባቢ ፀጋን በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

በብልጽግና ፓርቲ የተዘጋጀ የምርጫ ቅስቀሳና እጩዎችን የማስተዋወቂያ መድረክ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ እንሴኖ ከተማ ተካሄዷል።

በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ ውጤታማ ያደረገው የአካባቢ ፀጋን በማልማት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።


 

ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ኢንሼቲቮችን በመቅረፅ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና በዚህም ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ በየአካባቢው የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ልማቱ ትርፍ የማምረት ባህል እየዳበረ መምጣቱን ነው የገለጹት።

በዚህም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ከማሳደግ በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋትና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በአካባቢው በህዝቦች መካከል የኖረውን የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴትን በማጠናከር የተጀመሩ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ ፓርቲውን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው፤ በብልፅግና ፓርቲ የአካባቢን ፀጋን ለይቶ የማልማትና የመጠቀም እሳቤ በዞኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ትሩፋቶች የተገኙበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።


 

አርሶ አደሩ በመስኖ አልምቶ በመጠቀም ከራሱ አልፎ ለገበያ በማቅረብና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር ተጠቃሚነትን የበለጠ ለማሳደግ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብልፅግና ፓርቲ ጎን ሊቆሙ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ኸይሪያ ከድር ለአካባቢው ሰላም መስፈንና ለህዝቡ ተጠቃሚነት መረጋገጥ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ከፓርቲው ጎን መሆናቸውን ለማሳየት በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ስለመገኘታቸውም አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም