የአርብቶ አደሩን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶ አደሩን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሰመራ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
በአፋር ክልል በሚሌ ወረዳ አዳይቱ ከተማ በ50 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነባ ጤና ጣቢያ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ርእሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር በክልሉ የህዝቡን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የጤና፣ የትምህርት እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ለአገልግሎትም እየበቁ መሆኑን አንስተው በዛሬው እለት ለምርቃ የበቃው የጤና ተቋምም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።
የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ ያሲን ሐቢብ፤ በተለይም የእናቶችና ህፃናትን እንዲሁም የአርብቶ አደሩን የጤና አገልግሎት ማሳለጥ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዛሬው እለት ተገንብቶ የተመረቀው ጤና ጣቢያ በአዳይቱና አካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።