ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ውጭ ከላከው የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ውጭ ከላከው የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለአውሮፓ ሀገራት ከላከው የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሀይሉ የተራ፤ በክልሉ የኢንዱስትሪ ምርታማነትንና የገቢ አቅምን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በተለይ በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ወጭና ተኪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ኢንቨስት ለማድረግ ውል ከፈፀሙ 34 ድርጅቶች መካከል አሥሩ በምርት ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለአውሮፓ ሀገራት ከተላከ የአቮካዶ ዘይት ምርት ብቻ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ አልሚዎችም ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለዋል ብለዋል።
ፓርኩ የተሟላ መሰረተ ልማትና በዩኒየኖች በኩል ከአርሶ አደሩ ጥሬ ምርት መሰብሰብ የሚያስችል የተደራጀ ተቋማዊ አሰራር እንዳለው ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ ባላሀብት ዕድሉን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት የሆነውና በአቮካዶ ዘይት የተሰማራው የኢትዮ ፍሩት ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደጀኔ ጉታ በበኩላቸው ወደ 500ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያስገኘ ምርት ወደተለያዩ የአውሮፓ ገበያዎች መላካቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ የተሟላ መሰረተ ልማት እንዳለው ገልጸው ወቅታዊውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
የዋይ.ቢ.ኤም የአቮካዶ ዘይት ፋብርካ ሥራ አስኪያጅ ፀጋአብ መለሰ በበኩላቸው ባለፉት አራት ዓመታት ከ8 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያስገኘ ምርት ለውጭ ገበያ ከፋብሪካው መላኩን ገልጸዋል፡፡
ተግባሩን በማጠናከርም በተያዘው የምርት ወቅት ከ2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ የአቮካዶ ዘይት ወደ አውሮፓ ገበያ ለመላክ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው መሆኑ፣ የመንግስት ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በአካባቢው ያለው የአቮካዶ ምርት አቅርቦት በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በፓርኩ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ከመሟላታቸው ባለፈ በአካባቢው ጥሬ ምርትና የሰው ሀይል በበቂ ሁኔታ መኖሩ ለነባሩም ሆነ አዲስ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በ2012 ዓ.ም ወደ ሥራ የገባው የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ294 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው፡፡