ቀጥታ፡

ፔፕ ጋርዲዮላ ከ10 ዓመታት በኋላ ማንችስተር ሲቲን እንደሚለቅ ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የማንቸስተር ሲቲ ዋና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከእሁዱ የአስቶንቪላ የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ ክለቡን እንደሚለቅ ይፋ ሆኗል።

ማንቸስተር ሲቲ የአሰልጣኙን መልቀቅ  አረጋግጧል።

ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ባለፉት 10 የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመናት ክለቡን በመምራት ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ 17 ዋና ዋና ክብሮችን ማሳካት መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

የ55 ዓመቱ አሰልጣኝ የመጨረሻ ጨዋታውን እሁድ በኢትሃድ ስታዲየም ከአስቶንቪላ ጋር እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ማንቸስተር ሲቲ የአሰልጣኙ ውል ከመጠናቀቁ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለስንብቱ ዝግጅት እያደረገ እንደነበር ቢቢሲ ስፖርት በዘገባው አስታውሷል።

አሰልጣኝ ጋርዲዮላ ስለ ስንብቱ በሰጠው አስተያየት "የምለቅበትን ምክንያት አትጠይቁኝ፤ ምንም አይነት የተለየ ምክንያት ባይኖርም የመልቀቂያዬ ጊዜ መድረሱን ግን በውስጤ አውቀዋለሁ" ብሏል።

አክሎም "በዚህ ዓለም ላይ ዘላለማዊ የሚሆን ምንም ነገር የለም፤ ቢኖር ኖሮ እዚሁ እቆይ ነበር። ዘላለማዊ ሆኖ የሚቀረው ግን ስሜቱ፣ ሰዎቹ፣ ትዝታዎቹ እና ለክለቡ ያለኝ ፍቅር ብቻ ነው" ሲል ስሜቱን ገልጿል።

አሰልጣኙ ከሳምንት በፊት ከሲቲ የመጨረሻ ዋንጫውን በኤፍኤ ካፑ አንስቷል።

የ55 ዓመቱን ፔፕ ጋርዲዮላ ለመተካት ቀደም ሲል በማንቸስተር ሲቲ በረዳትነት የሰራውና የቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ቀዳሚው እጩ መሆኑ ተጠቁሟል።

የጋርዲዮላ ከክለቡ የመልቀቅ ዜና ይፋ የሆነው ማንቸስተር ሲቲ የ2025-26 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በአርሰናል ከተቀማ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ማክሰኞ  ከቦርንማውዝ ጋር አቻ መለያየቱን ተከትሎ አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን መሆን መቻሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም