በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የበጋ ስንዴ ልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ጉዞ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የበጋ ስንዴ ልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ጉዞ እያገዘ ነው
ጭሮ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የስንዴ ሰብል በበጋ መስኖ በማልማት እየተገኘ ያለው ውጤት፣ ማኅበረሰቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የተጀመረውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እያገዘ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ገለፀ።
በፅህፈት ቤቱ የስንዴ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማቱ ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ የኑሮ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።
ከዚህ ቀደም በበቆሎና በሌሎች ሰብሎች ይሸፈን የነበረ እንዲሁም ለግጦሽ ይውል የነበረ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአሁኑ ወቅት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህ ወቅት ዓመታዊ ምርት ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል በላይ የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 6 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።
ባለሙያው አክለውም፣ አርሶ አደሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችንና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት መጠቀም መቻሉ ለምርት መጨመር ዋነኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አብራርተዋል።
የቦኬ ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሳሚያ መሐመድ በበኩላቸው፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ አርሶ አደሮች ለልማት አመቺ የሆኑ መሬቶችን በበጋ ስንዴ እንዲያለሙ የተሰራው ስራ የአርሶ አደሩን ኑሮ እየቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
ልማቱ እንደተጀመረ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 25 ኩንታል ምርት በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ማድረስ ተችሏል ያሉት ወይዘሮ ሳሚያ፣ ለዚህ ስኬት የአርሶ አደሩ የግብዓት አጠቃቀም ማደግ እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልፀዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት ምርት ተገቢውን ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ ከዩኒየኖች ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩንና ዩኒየኖቹ ምርቱን ከአርሶ አደሩ መኖሪያ ቤት ድረስ ሄደው እንደሚረከቡ አስረድተዋል።
የቦኬ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት ያህያ አደም በሰጡት አስተያየት፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብም እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ በመሆኑ ኑሯቸው መሻሻሉን አብራርተዋል።
በጡሎ ወረዳ ኢፋ አንዶዴ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ጌታቸው አበበ በበኩላቸው፤ በየዓመቱ በበጋ መስኖ ልማት ግማሽ ሄክታር ማሳ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በየዓመቱ ከመቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውንና የተገኘውን ገቢ ለግብርና ግብዓት ግዢ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።