ቀጥታ፡

ወቅቱ የሚበጀንን ፓርቲ የምንለይበትና ካርዳችንን ለምርጫው የምናዘጋጅበት ነው - የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች

አሶሳ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ ወቅቱ የሚበጀንን ፓርቲ የምንለይበትና ካርዳችንን ለምርጫው የምናዘጋጅበት ነው ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በክልሉ አሶሳ ዞን መንጌ ወረዳ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በምርጫው ዕለት ለሀገር ልማት፣ ሰላምና ብልፅግና ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት ለመምረጥ ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል። 

በምርጫው ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን የመራጭነት ካርድ በአግባቡ በመያዝ የድምጽ መስጫ ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ጀማል ኡመር እና ኢሳ ሙሐመድ ምርጫው ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር እና የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ መንግስት ለመመስረት ያግዛል ብለዋል።

የመራጮች ምዝገባ ጊዜ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን እና የድምፅ መስጫ ቀንን በታላቅ ዝግጁነት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ እንዲሆን መራጮች በድምፅ መስጫው ዕለት ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መመሪያ መተግበር እንዳለባቸውም ነዋሪዎቹ መክረዋል።

ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ሐናን አልሂሴን እስከአሁን የነበረው የቅድመ ምርጫ ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ገልጸው፥ ዜጎች ያወጡትን የመራጭነት ካርድ በድምፅ መስጫው ቀን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በምርጫ መሳተፍ በዜጎች ይሁንታ ያገኘ መንግስት ለመምረጥ ወሳኝ በመሆኑ ሁላችንም ዕድሉን በመጠቀም በምርጫው መሳተፍ አለብን ነው ያሉት።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የምርጫ ክርክር የድምጽ መስጫው ቀን መምረጥ የሚያስችላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመለየት እንዳስቻላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አልፋድል በደዊ ናቸው።

አሁን ያለው ወቅት መራጮች የቀረቡትን የፖለቲካ አማራጮች በጥንቃቄ በመገምገም የሚመርጡትን ፓርቲ ከወዲሁ የሚለዩበት እና የተሰጣቸውን የመራጭነት ካርድ በአግባቡ ጠብቀው የሚቆዩበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም