በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎች ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎች ተሸፍኗል
ጋምቤላ ፤ግንቦት 14/ 2018 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎችና የጓሮ አትክልቶች መሸፈኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድሮው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ180 ሺህ 850 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት፣ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል።
በእስካሁኑ ሂደት በምርት ዘመኑ ለማልማት ታቅዶ ከነበረው መሬት ውስጥ ከ39 ሺህ 840 ሄክታር በላይ የሚሆነው ማሳ ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎች መሸፈኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ኦቾሎኒ፣ አኩሪ አተር እንዲሁም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ለማልማት ከታቀደው መሬት መካከል 99 ሺህ ሄክታሩ በሜካናይዜሽን ታግዞ ለማልማት እንዲቻል የእርሻ ትራክተሮች ስምሪት መደረጉንም አስታውቀዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ከ36 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በምርት ዘመኑ ለማልማት የታቀደው መሬት ሙሉ በሙሉ በዘር እንዲሸፈንና አንድም ማሳ ሳይታረስ እንዳይቀር የአመራርና የባለሙያዎች ስምሪት መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።
በዚህም ለአርሶና አርብቶ አደሮች የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በልማት ፕሮጀክቶች በመታገዝ፤ የየአካባቢውን ስነ-ምህዳር መሰረት ያደረገ የበቆሎ፣ የማሽላና የሩዝ ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ ቀርቦ መሰራጨቱንም አቶ አንድሮው ገልጸዋል።
የአርሶና አርብቶ አደሩን ግንዛቤ በማጎልበት፣ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በስፋት እንዲጠቀም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል።
የኢታንግ ልዩ ወረዳ አርሶ አደር ጀምስ ቦት በሰጡት አስተያየት፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከአራት ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሦስት ሄክታር ብልጫ እንዳለውና የእርሻ መሬታቸውን ለማስፋት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከስድስት ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎ፣ በማሽላና በሰሊጥ ሰብሎች ለማልማት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጎግ ወረዳ ነዋሪው ወጣት አርሶ አደር ኡሞድ ኡኮች ነው።
በአሁኑ ወቅት ቀድሞ የሚዘራው የበቆሎ ሰብል የተወሰነ ማሳቸውን መሸፈኑን የገለጹት ወጣቱ አርሶ አደር፤ በቀጣይም ቀሪዎቹን የእርሻ መሬቶች በሌሎች ሰብሎች ለመሸፈን አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።