ቀጥታ፡

ግብርናና ቱሪዝም የሚያስገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማላቅ እየተከናወኑ ያሉ የምርምር ስራዎች ይጠናከራሉ

ጂንካ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፡- ግብርናና ቱሪዝም የሚያስገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማላቅ እየተከናወኑ ያሉ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በጂንካ ዩኒቨርስቲ ''ግብርናና ቱሪዝም ለአካታችና ለዘላቂ ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ሁለተኛው አለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።


 

በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርስቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር) በምርምር ኮንፈረንሱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ግብርናና ቱሪዝም ለዘላቂ የልማትና የኢኮኖሚ እድገት ግብ ስኬታማነት የጀርባ አጥንት ናቸው ብለዋል።

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ተልዕኮ ባሻገር ግብርናን እና ቱሪዝምን የምርምር እና የልህቀት ማዕከል ለማድረግና ዘርፎቹን ለማህበረሰብ ለውጥ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማፍለቅ ከቱሪዝም እና ከግብርናው ዘርፍ የሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም እንዲጎለብት ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኮንፈረንሱ ልምድና ተሞክሮን በመቀመር በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝም አመልክተዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ሀገራችን ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ሀገራዊ ራዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት ችግር ፈቺና መፍትሔ አመላካች የምርምር ውጤቶች እና ተጨባጭ ማሳያዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማትም በተለይ በቱሪዝምና በግብርናው መስክ የምርምር ውጤቶችን በማፍለቅ ለተያዘው ዘላቂ ልማትና እድገት ግብ መሳካት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

በመድረኩ የተጋበዙት የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ሻውና ሎቶስኪ (ዶ/ር)፥ ከ23 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በቅርበት እንደሚያውቋት አንስተዋል።

በሙርሲ ባህል እና አኗኗር ላይ ጥናቶችን ያከናወኑት ተመራማሪዋ፥ አካባቢው ዕምቅ የቱሪዝም ሀብት ያለበት እንደሆነም አመልክተዋል።

በአካባቢው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙ ደግሞ እነዚህን እምቅ ሀብቶች በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛል ነው ያሉት።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር ለዞኑ ማህበረሰብ ለውጥ በምርምር የተደገፉ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማፍለቅ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።


አካባቢው እምቅ የግብርናና የቱሪዝም ሀብት ያለበት በመሆኑ ይህንን ሀብት በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል ዩኒቨርሲቲው ሙያዊ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

በምርምር ኮንፍረንሱ ላይም አለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ተሞክሮዎችን የሚያስቃኙ የጥናት ውጤቶች ይቀርባሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም