የአካባቢያችንን ፀጋ በመጠቀም የነበረብንን የስርዓተ ምግብ ችግር ፈተናል - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ፀጋ በመጠቀም የነበረብንን የስርዓተ ምግብ ችግር ፈተናል
ሰቆጣ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግስት በተደረገልን ድጋፍ የአካባቢያችንን ፀጋ በመጠቀም የነበረብንን የስርዓተ ምግብ ችግር ለመፍታት ችለናል ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጋዝጊብላ ወረዳ የመስቀሎ ቀበሌ እናቶች ገለፁ።
በጋዝጊብላ ወረዳ መስቀሎ ቀበሌ የሚገኘው የግቢው መንደር "የስርዓተ ምግብ ሞዴል" ሆኖ ተመርጧል።
የመንደሯ እናቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በመንግስት በተደረገልን ድጋፍ ተነሳስተን የአካባቢያችንን ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም በመቻላችን የነበረብንን የስርዓተ ምግብ ችግር ለመፍታት ችለናል ብለዋል።
ከመንደሯ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ብዙወይ ወዳጅ፤ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት ድጋፍ በአካባቢያቸው ያለውን ውሃ በመጠቀም የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት፣ ዶሮ በማርባትና ንብ በማነብ የነበረባቸውን የስርዓተ ምግብ ችግር መፍታታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ አትክልት፣ እንቁላል፣ ማርና የስጋ ተዋጽኦዎችን በማምረት ልጆቻቸውን አሰባጥረው በመመገብ ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተደረገልን ድጋፍ የስርዓተ ምግብ አቅማችንን በማሳደግ ልጆቻችንን ከመመገብ ባሻገር የቤተሰባችን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል አድርጓል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ባያት ፀሃዩ ናቸው።
የጓሮ አትክልትን፣ ከእንቁላልና ወተት ጋር በማሰባጠር ህፃናት ልጆቻቸውን በአግባቡ በመመገባቸው የተሻለ የእድገት ሁኔታ እንዲኖራቸው ማስቻሉን አስረድተዋል።
"አሁን ላይ የልጆቻችንን ምግብ በጓሯችን ላይ መሸፈን ችለናል" የሚሉት ወይዘሮ ባያት የአካባቢያቸውን ንፅህና በመጠበቅ የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ጤንነት እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ወይዘሮ አልማዝ ጌታሁን በበኩላቸው በተሰጣቸው የክህሎት ስልጠና መሰረት ሶስት ልጆቻቸውን በንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦችን በማሰባጠር እየመገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት በተደረገላቸው የጓሮ አትክልት ዘርና የወተት ፍየሎች ድጋፍ የስርዓተ ምግብ አቅማቸውን እያጎለብቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመንደሯ የሚገኙ እናቶች በስነ ተዋልዶና በልጆቻቸው ጤንነት ዙሪያ የሚወያዩበት ስርዓት ተፈጥሮ በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ወይዘሮ አልማዝ አስረድተዋል።
የጋዝጊብላ ወረዳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ተወካይ አስተባባሪ አቶ ደስታየ ደባሽ እንደገለፁት፤ በግቢው መንደር 60 እናቶች በስርዓተ ምግብ ማሻሻል ብቁ መሆናቸው ተረጋግጦ የሞዴል መንደር ተመስርቷል ብለዋል።
በግቢው መንደር የተጀመረውን የስርዓተ ምግብ ማሻሻል እንቅስቃሴ በሌሎች ቀበሌዎችም የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ሞገስ ሃይሌ እንዳሉት መምሪያው ከሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህብረተሰቡን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየሰራ ነው።
በሥርዓተ ምግብ ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ በ69 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ 82 ሞዴል መንደሮች መመስረታቸውን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ ሁለት መንደሮች ስኬታማ በመሆናቸው ለምረቃ በቅተዋል ብለዋል።