ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ የልማት ስትራቴጂዎች የሕዝብን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የቻሉ ናቸው-ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

ሚዛን አማን፣ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ የልማት ስትራቴጂዎች የሕዝብን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የቻሉ መሆናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ሚዛን አማን ከተማ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ አካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፥ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የተገበሩ የልማት ስትራቴጂዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቻሉ ናቸው።

በተለይ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ በቱሪስት መዳረሻ ልማት፣ በማዕድንና በግብርናው ዘርፍ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፤ ፓርቲው ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ቃልን በተግባር የሚያረጋግጡ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት፣ እንዲሁም የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በማስፈን ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተጋ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን በመጠገን የዞኑን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ያሉት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ናቸው።

ሰው ተኮር ተግባራትን በማከናወን የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቀጣይም በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተሳተፉት የፓርቲው ደጋፊዎች መካከል አቶ በላይ ቡላብ እና አቶ ዓለማየሁ ደኳብ በበኩላቸው፤ ፓርቲው አሻጋሪ ሐሳቦችን በመያዝ አካባቢያቸውን በማልማት የሕዝብ አለኝታነቱን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም