ቀጥታ፡

ሁለገብ የገበያ ማዕከሉ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል-ሸማቾች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ሁለገብ የገበያ ማዕከሉ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻሉን ሸማቾች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተገነቡ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠርና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ኢዜአ በለሚ ኩራ የገበያ ማዕከል ባደረገው ቅኝት ሸማቾች በማዕከላቱ ሁሉንም ዓይነት ምርቶች በማግኘት ከእንግልት መዳናቸውን ገልጸዋል።

በማዕከሉ የሚገኙ የምርቶች ዋጋም ከማዕከላቱ ውጭ ከሚገኙ ገበያዎች አንጻር ሰፊ ልዩነት ያለውና ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።

በለሚ ኩራ የገበያ ማዕከል ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ አሊ እንድሪስ፤ የማዕከሉ መገንባት ጥራታቸውን የጠበቁ የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ሁሉንም ዓይነት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በአንድ ማዕከል ማግኘታቸው የገበያ አማራጭ እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።

የግብርና ምርቶችን በአቅራቢያችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት የምንችልባቸው የገበያ ማዕከላት ወደ አገልግሎት መግባታቸው ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል ያሉት አቶ ባይሳ ግርማ ናቸው።

በተጨማሪም የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች በየቀኑ የሚገቡ ጥራት ያላቸው በመሆናቸው ለጤና ጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በገበያ ማዕከሉ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶች አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ ማግኘታቸውን ጠቅሰው ከውጭ ገበያ ጋር ሰፊ ልዩነት እንዳለው የገለጹት ደግሞ አቶ ክብሮም ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡

በመዲናዋ አራቱም ማዕዘናት የተገነቡት የገበያ ማዕከላት ከደላላ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆኑና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ በማስቻል ላይ ይገኛሉ።

በለሚ ኩራ የገበያ ማዕከል ያነጋገርናቸው አምራች አብርሃም ንጉሴ እንዳሉትም፤ መንግስት የመስሪያ ቦታውን በነጻ በመስጠት ላደረገላቸው ትልቅ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በዚህም ጥራት ያላቸውን የግብርና እና የአትክልት ምርቶች ከውጪው የገበያ ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ መሰረት አቦባሬ እና አቶ ቶልቻ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ምርቶቹ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የሚቀርቡ በመሆናቸው የገበያ ንረትን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ህብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ በማገልገል ገበያውን ለማረጋጋት ያስቻለ በመሆኑ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የከተማዋ ነዋሪዎችም በማዕከላቱ በደስታ እየተገበያዩ ይገኛሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም