ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር እያደገ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር እያደገ መምጣቱን በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና ዱባይ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱም ተገልጿል።


 

በዱባይ የንግድ ምክር ቤት የተዘጋጀው የዱባይ - ኢትዮጵያ ቢዝነስ ትብብር ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል ናት።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ለኢንቨስትመንት የተመቸ ስነ ምህዳር፣ የጂኦግራፊ አቀማመጥ ለስራ ብቁ የሆነ የሰው ሀይል ያላት ምቹ የቢዝነስ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የወጣቶች ምድር የአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን አፍሪካውያን የገበያ መግቢያ በርና የምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉንም የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅፋቶችን በማስወገድ ኢትዮጵያን ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቸች ሀገር አድርጓታል ብለዋል።

የመስኮት የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ በተሟላ መሰረተ ልማት ፈጣንና ቀልጣፋ የንግድ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉ የአየር መንገድ፣ የባቡርና ተሽከርካሪ የተሳለጠ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት መዘርጋቷን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር እያደገ መሆኑን ገልጸው፣ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ አድርገውታል ብለዋል።

የዱባይ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሞሐመድ አሊ ራሸድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወሳኝ የንግድ ኢንቨስትመንትና የገበያ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ መልክዓምድር ላይ የምትገኝ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግብርናና መሰል መስኮች ትብብራቸው እያደገ በመምጣቱ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬት የኢትዮጵያ ካምፓኒዎች መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።

በዱባይ ከአንድ ሺህ 660 በላይ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በንግድ፣ ሪልስቴት፣ ሎጂስቲክስና መሰል ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና ዱባይ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ገልጸው፤ የዛሬው ፎረምም የሁለቱን ሀገራት ኩባንያዎች ንግድና ኢንቨስትመንት ያጠናክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም