ቀጥታ፡

የጅግጅጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ከ672 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የጅግጅጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በምረቃው ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ፣የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን ፣የክልሉ የመንገዶች ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢድሪስ ሙሴ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ መሀመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የጅግጅጋ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ፕሮጀክት የከተማውን የንግድ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ያስችላል።


 

መንገዱ ህብረተሰቡን ጥራት ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር የከተማውን ገፅታ በመለወጥ ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።

በክልሉ ከለውጡ ወዲህ የተከናወኑ ሁለተናዊ የልማት ስራዎችን በእጥፍ በማሳደግ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የጅግጅጋ ከተማ ተለዋጭ የመንገድ ፕሮጀክት የጅግጅጋ ከተማን ልማትና ዕድገት በማፋጠን በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ የመንገድ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከፍተኛ አስተዋኦ ላበረከቱ ተቋማት እና ለክልሉ መንግስት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የመንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን አስተዳደሩ ሀገራዊ የመንገድ መሰረተ ልማት ዕቅድን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የጅግጅጋ ከተማ ተለዋጭ የመንገድ ፕሮጀክትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ተግባራዊ የተደረገው የመንገድ ፕሮጀክቱ በይርጋለም የመንገድ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት የተገነባ መሆኑንም ተገልጿል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 7 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 30 ሜትር ስፋት ያለውም መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ዘገባ ያሳያል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም