ቀጥታ፡

በጅማ ዞን የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ማህበራዊ ችግሮቻችንን ፈተዋል-የዞኑ ነዋሪዎች

ጅማ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን የተገነቡ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን ምላሽ የሰጡና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን የፈቱ መሆናቸውን የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በዞኑ በበጀት ዓመቱ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች መሠረት ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት በመሆን ላይ ይገኛሉ።

በዞኑ ቦቶር ጦላይ ወረዳ በዋዩ ከተማ የሚገኘው የወዴሳ ወንዝ ድልድይ ባለመሠራቱ ምክንያት ባለፉት ዓመታት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ትልቅ ፈተና እንደነበረ የገለጸችው ተማሪ ሽቶ ተፈራ ናት።

አሁን ላይ ድልድዩ ተሠርቶ በመጠናቀቁ እሷም ሆነች የአካባቢው ነዋሪዎች ያለስጋት ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻቸውን ለማከናወን መቻላቸውን ገልጻለች።

የወረዳው ነዋሪዎች የሆኑት አቶ ደርበው ጌታቸው እና አቶ ጂሃድ ጫላ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ወንዙን ለመሻገር በነበረው አዳጋች ሁኔታ ምክንያት ከብቶች ይወሰዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህም ባለፈ የታመሙ ሰዎችንና ነፍሰ ጡር እናቶችን በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋም ማድረስ ባለመቻሉ የሰዎች ሕይወት ያልፍ እንደነበር አስታውሰው፣ የድልድዩ መገንባት ትልቅ እረፍትና ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዩሱፍ ሻሮ በዞኑ ባለፉት ዓመታት ለሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 9 ድልድዮችን ጨምሮ 1 ሺህ 954 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ የሕዝቡን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የገጠር መንገድ ጥገና መደረጉን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤቶች፣ የሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላዎች፣ ድልድዮች እና የገጠር መንገዶች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት በጀትና በሕዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ በመሆናቸው በቀጣይም የነዋሪውን ጥያቄ የሚመልሱ ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም