ቀጥታ፡

መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እያደረገልን ባለው የተቀናጀ ድጋፍ በንብ ሃብት ልማት ውጤታማ ሆነናል

ዲላ፤ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፡-  መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እያደረገልን ባለው የተቀናጀ ድጋፍ በንብ ሃብት ልማት ውጤታማ ሆነናል ሲሉ ንብ አናቢዎች ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የንብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ሀገር አቀፍ የማር ምርትና የንብ ማነቢያ ግብዓቶች ኤግዚቢሽን በዲላ ከተማ ተካሄዷል።

በወቅቱም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንብ ሃብት እምቅ አቅምን አውጥቶ ለመጠቀም እገዛ እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

በተለይ ለዘርፉ የሚደረግ የግብዓት፣ የሙያና የገበያ ትስስር ድጋፍ የአልሚዎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ በርካቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በር የከፈተ መሆኑም ተገልጿል።

ለዚህም ከሌማት ትሩፋት ትግበራ በፊት በዓመት 146 ሺህ ቶን ብቻ የነበረው ሀገራዊ የማር ምርት ዛሬ በ9 ወር ብቻ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ከ304 ቶን መሻገር ችሏል።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አልሚዎችም መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እያደረገላቸው ባለው የተቀናጀ ድጋፍ በንብ ሃብት ልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን መንገሻ ወረዳ ነዋሪው ቲቶ ሐዋርያት ለኢዜአ እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት 300 ቀፎዎችን በመያዝ ወደ ንብ ማነብ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓመት ሶስት ጊዜ ምርት በመሰብሰብ ከ8 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተጣራ ማር ለገበያ በማቅረብ እስከ 700 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከማር ምርት ባሻገር ከሰም ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን አንስተው ይሄም የሌማት ትሩፋት የተቀናጀ የመንግስት ድጋፍ ውጤት ነው ብለዋል።

ለአናቢዎች የሚደረግ የግብዓት፣ የሙያና የገበያ ትስስር ድጋፎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እንዳነሳሳቸው የገለፁት ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ላሊበላ ወረዳ ነዋሪ ካሳዬ አየነው ናቸው።


 

65 ዘመናዊ ቀፎዎችን ይዘው ወደ ልማቱ መግባታቸውን አንስተው ከአንድ ቀፎ በዓመት 30 ኪሎ ግራም ማር እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

ያገኙትን ምርት ለገበያ በማቅረብ በዓመት ከ300 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ውጤታማ መሆናቸውን አንስተው ኤግዚቢሽኑ የገበያ አማራጭ በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን የማንቻ የንብ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት መሰለች በርገኒ በበኩሏ የንብ ልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዳሸጋገራቸው ጠቅሳለች።

ከሁለት ዓመት በፊት አስር ሆነው በ250 ቀፎ የጀመሩት የንብ እርባታ ከማር ምርት ባለፈ በንግስት ንብ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግራለች።

በዚህም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች መትረፋቸውን ጠቅሳ ለውጤታማነታቸው የመንግስት ድጋፍ መሠረት መሆኑን ገልጻለች።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ደጀኔ ታከለ በበኩላቸው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ አልሚዎችን በማነቃቃትና አዲስ በመቀላቀል የምርት ጥራትና መጠንን አሳድጓል።


 

ለዚህም ከሌማት ትሩፋት ትግበራ በፊት በዓመት 146 ሺህ ቶን ብቻ የነበረው ሀገራዊ የማር ምርት መጠን ዘንድሮ በ9 ወር ብቻ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ከ304 ቶን መሻገሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም