ነጋሪ መፅሔት "የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት'' በሚል ዐቢይ ጉዳይ ለንባብ በቅታለች - ኢዜአ አማርኛ
ነጋሪ መፅሔት "የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት'' በሚል ዐቢይ ጉዳይ ለንባብ በቅታለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ) ፦ነጋሪ መፅሔት "የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት'' የሚል ዐቢይ ጉዳይና ሌሎች ከሀገር እስከ ዓለም ወሳኝ አጀንዳዎችን ይዛ ለንባብ በቅታለች።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ የምትታተመው "ነጋሪ" መጽሔት በ8ኛ ዓመት 33ኛ ዕትሟ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዐቢይ ጉዳይ በማድረግ "የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት" በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ዳሰሳን ይዛለች።
መፅሔቷ የኢትጵያን የምርጫ ታሪክ ከትናንት እስከዛሬ፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እስከ ምርጫ ተቋማት ያለውን የተሟላ ዝግጁነት በወፍ በረር ታስቃኛለች።
ኢትዮጵያ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆኗን በተመለከተ በዝርዝር ዳስሳለች።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ለጀመረችው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በተመለከተም በስፋት ለአንባቢያን አሰናድታለች።
በሌላ በኩል በመፅሔቷ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ከ2025 አፈጻጸም እስከ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግቦች ከብሔራዊ የልማት አጀንዳዎች ጋር በማስተሳሰር በጥልቀት ተተንትኗል።
39ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ከአጀንዳ 2063 አህጉራዊ ግቦች አንጻር በመፈተሽ አንኳር አጀንዳዎችን አንስታለች።
ኢትዮጵያና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን በመቃኘት፣ የስምምነቱ ዓላማና ፋይዳዎችን በዝርዝር ዳስሳለች።
ሀገር በቀል እውቀት ላይ ባተኮረው ወሳኝ ዓምዷም የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በተመለከተ አስታራቂው መንገድ በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አቅርባለች።
ከኢትዮጵያ እስከ ዓለም የህዋ ሣይንስና ጂኦስፓሻል ህልሞች፣ ሙከራዎች፣ ስኬቶች፣ አሁናዊ የቴክኖሎጂው ዝማኔና የሀገራችንን የዘርፉ መሻት ከየት ወደየት በጥልቀት ቃኝታለች።
ከተፈጥሮ እስከ ሰው ሰራሽ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች ለኢትዮጵያ ጸጋ ናቸው። ለዘመናት ተሸፍኖ የቆየውና ከለውጡ ወዲህ የተገለጠው የኢትዮጵያ ውበትና ቱሪዝም የነጋሪ ሌላኛው ጉዳይ ሆኗል።
መፅሔቷ ድንበር ያልገደበው ማዕከል በሚል ርዕሰ ጉዳይ በሀገራችን የህክምና ልህቀት የደረሰበትን ደረጃና በዘርፉ ቁልፍ የሚባሉ ጉዳዮችን አንድን ስመ ጥር የህክምና ተቋም በአብነት በማንሳት በሰፊው አትታለች።
ነጋሪ ሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም በጥልቀት በመዳሰስ ለአንባቢዎቿ እነሆ ትላለች።