አዲስ አበባ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች የሚገነቡባት ከተማ ሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች የሚገነቡባት ከተማ ሆናለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ) ፦ አዲስ አበባ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት የሚገነቡባት ከተማ እንደሆነች ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ያቀዳቸውንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን አስመርቋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ በዚሁ ወቅት፤ በማህበረሰብ ተሳትፎ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ዕውን ሆነዋል።
ለአብነትም በማህበራዊ ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት ለትውልድ ግንባታ መሠረት የሚጥሉ የቅድመ-አንደኛ፣ አንደኛ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የሕፃናት ማቆያዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በጤና ዘርፍም የተቋማትን አክሞ የማዳንና የበሽታ መከላከል አቅም የሚያጎለብት ውጤታማ መሠረተ ልማትና ግብዓት የማሟላት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የለውጥ አብዮትም የመንገድና ስፖርት ማዘውተሪያን ጨምሮ መዲናዋን ፅዳትና ውበት ያላበሱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።
አዲስ አበባ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት የሚገነቡባት ከተማ መሆኗን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በመፈፀም ተወዳዳሪና ምቹ ከተማ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማው የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት መገንባታቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በዛሬው ዕለት የሕፃናት ማቆያዎችን ጨምሮ የቅድመ-አንደኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች የልማት ሥራዎች ለምርቃት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።